የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የህጻናትን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የህጻናትን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ

ባህርዳር፤ ህዳር 2/2017(ኢዜአ)፡- የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።
"ህጻናት የሚሉት አሏቸው እናዳምጣቸው" በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ የህጻናት ቀን በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተከብሯል።
የቢሮው ሀላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ህጻናት መብታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲያድጉ የሁሉም አካል ድጋፍና ሀላፊነት ወሳኝ ነው።
በቴክኖሎጂ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚ የበለፀገች ሀገር ለመገንባት ህጻናት ላይ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ የሁሉም ህብረተሰብ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ቢሮው የህጻናትን መብትና ደህንነት የመጠበቅ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ህጻናት የመናገር ነጻነታቸውን እንዲያዳብሩ ክልላዊ የህጻናት ፓርላማ ተቋቁም እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የህጻናትን መብትና ደህንነት ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የብሔር ብሔረሰቦችን ባህልና ቋንቋ እንዲያውቁና የፌዴራሊዝም ስርዓትን ምንነት ተረድተው እንዲያድጉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ የህጻናትን ፓርላማ የማጠናከር፣ የመደገፍና ልምድ የማጋራት ሀላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
ለህጻናት መብትና ደህንነት መከበር በሀላፊነት እየሰሩ የሚገኙ አጋርና ባለድርሻ አካላት እያደረጉት ያለውን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ህጻናት ፓርላማ አፈ ጉባኤ ህጻን ተምኪን የሐ እንደገለጸችው፤ ህጻናት መብቶቻቸው እንዲከበሩና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ሁሉም ሊረባረብ ይገባል።
ለዚህም ህብረተሰቡ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክታለች።
አለም አቀፍ የህጻናት ቀን የሚከበረውም ለህጻናት መብትና ደህንነት ጥበቃ ትኩረት ለመስጠት እንደሆነ ጠቅሳ፤ እኛ ህጻናትም የድርሻችንን መወጣት ይገባናል ብላለች።
በዕለቱ በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ላመጡ ህጻናት የገንዘብና የእውቅና ሽልማት የተሰጠ ሲሆን፣ በባህር ዳር አጼ ሰርፀ ድንግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚማሩ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስና አልባሳት ድጋፍ ተደርጓል።
በመድረኩ የክልል አመራር አባላት፣ የህጻናት ፓርላማ አባላትና ባለድርሻና አጋር አካላት ተሳትፈዋል።