የኢትዮጵያ ሕንጻ ረቂቅ አዋጅ በግንባታ ዘርፍ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሔ በማጀበት ረገድ ሚናው የጎላ ነው- ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሕንጻ ረቂቅ አዋጅ በግንባታ ዘርፍ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሔ በማጀበት ረገድ ሚናው የጎላ ነው- ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሕንጻ ረቂቅ አዋጅ በግንባታ ዘርፍ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሔ በማጀበት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የሕንጻ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።
ነባሩ አዋጅ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ የዋለ ሲሆን፤ በዘርፉ ያለውን እድገትና ለውጥ መሰረት በማድረግ አዲስ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
በስራ ላይ የቆየው አዋጅ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተዘጋጀ ቢሆንም ወደ ስራ ሲገባ ግን የየአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ያካተተ ባለመሆኑ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
የግንባታ ጥራትና የሀብት ብክነትም በዘርፉ የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በሰጡት ማብራሪያ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን እድገት ለማሳለጥ ብሎም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩም ዘርፉን ለማጠናከር አዳዲስ ሀሳቦች ገቢራዊ በማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታን በተመለከተ ብሔራዊ ስታንዳርድ ተዘጋጅቶ ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መሰጠቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በተደጋጋሚ የሚነሱና ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለይቶ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማመላከት ረገድ ረቂቅ አዋጁ ዘርፈ ብዙ ሚና እንደሚኖረውም አብራርተዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር አባል አቶ ማህደር ገብረመድህን በዘርፉ አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ጉዳዮች በአዋጁ መካተቱ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።
ይሁንና ለአካል ጉዳተኞች ተብለው የሚገነቡ ግንባታዎች በአግባቡ አገልግሎት እየሰጡ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ ሊፈተሽ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሌላኛው የማህበሩ አባል አርክቴክት በኃይሉ ጸጋዬ በበኩላቸው ግንባታ ከመጀመሩ በፊት ለዲዛይን ስራ በቂ ጊዜ መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ተወካይ ግርማ ሀብተማሪያም እንዳሉት፤የመሬት መንቀጥቀጥን ጨምሮ የሚከሰቱ አደጋዎችን መቋቋም የሚችል ግንባታ ያስፈልጋል።
በዚህ ረገድ አዋጁ መሰል ጉዳዮችን ማካተት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን(ዶ/ር) ዲዛይንን በጥራት ማከናወን የበጀት ብክነትን ከመቀነስ ባለፈ የግንባታ መራዘምን በማስቀረት ለግንባታዎች ውጤታማነት አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ግንባታዎች ከመካሄዳቸው በፊት የአዋጭነት ጥናት ወጥ በሆነ መልኩ ማካሄድ የሚያስችል አሰራር መዘርጋትም ልዩ ትኩረት እንደሚፈልግ አመልክተዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፤ በአስረጂ መድረኩ የተነሱ ሃሳቦች በግብዓትነት ተወስደው ቀጣይ ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።