የፀረ-አበረታች ቅመሞች የሕግ ጥሰት በፈፀሙ አትሌቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የፀረ-አበረታች ቅመሞች የሕግ ጥሰት በፈፀሙ አትሌቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2017(ኢዜአ)፦ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የሕግ ጥሰት በፈፀሙ አትሌቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ከአበረታች ቅመሞች ነጻ የሆነ ስፖርት ለመፍጠር የጀመረችውን እርምጃ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ገልጿል።
አትሌት ሕብስት ጥላሁን አስረስ፤ አትሌት ሳሙኤል አባተ ዘለቀ እና አትሌት ፀሐይ ገመቹ በያን የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግ በመጠቀም የሕግ ጥሰት መፈጻማቸው መረጋገጡን ገልጿል።
አትሌት ፀሐይ ገመቹ በያን በተደረገላት የአትሌት ባይሎጂካል ፖስፖርት (ABP) ምርመራ አበረታች ቅመም መጠቀሟ የተረጋገጠ ሲሆን ከእ.አ.አ November 30/2024 ጀምሮ ለአራት ዓመታት በማንኛውም የስፖርት ውድድር እንዳትሳተፍ እና ከ2020 እስከ November 30/2024 ጀምሮ ያስመዘገበችው ውጤት እንዲሰረዝ ቅጣት መጣሉን አመልክቷል።
እንዲሁም አትሌት ሕብስት ጥላሁን አስረስ ቻይና ሀገር ውስጥ በነበረው ውድድር ላይ በተካሄደው ምርመራ “Triamcinolone acetonide” የተባለውን የተከለከለ ንጥረ ነገር መጠቀሟ የተረጋገጠ ሲሆን ከእ.አ.አ June 3/2024 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት በማንኛውም የስፖርት ውድድር እንዳትሳተፍ እገዳ ተጥሎባታል።
በተመሳሳይ መልኩ አትሌት ሳሙኤል አባተ ዘለቀ እ.ኤ.አ February 29/2023 በተካሄደው ምርመራ “EPO” (Erythropoietin) የተባለውን የተከለከለ ንጥረ ነገር መጠቀሙ በመረጋገጡ ከእ.ኤ.አ April 17/2024 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት በማንኛውም የስፖርት ውድድር እንዳይሳተፍ እገዳ እንደተጣለበት ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
በቀጣይም በኢትዮጵያ በየደረጃው የሚደረገው ምርመራና ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ባለስልጣኑ ገልጿል።
የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመጠቀምም ይሁን በተለያዩ መልኩ የፀረ-ዶፒንግ የሕግ ጥሰት በሚፈፅሙ አትሌቶችና በሚተባበሩ ሌሎች ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው የእርምት እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።