ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ በከተማ ግብርና ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ምርቶች ተሸፍኗል - የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በከተማ ግብርና ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ምርቶች መሸፈኑን የከተማ አስተዳደሩ የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን አስታወቀ።

በአዲስ አበባ የከተማ ግብርናን በማስፋፋትና በማጠናከር ነዋሪዎች የራሳቸውን ፍጆታ እንዲሸፍኑና ገቢያቸው እንዲሻሻል አድርጓል።

በተለይ በሰብል፣ በእንስሳትና በጓሮ አትክልት ልማት እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች የእለት ፍጆታን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ለዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸውና ገቢ እንዲያገኙ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ነው።

የአስተዳደሩ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፋሩቅ ጀማል ለኢዜአ እንዳሉት፤ የከተማ ግብርና የበርካታ ዜጎችን ህይወት እየቀየረ ነው።


 

በመዲናዋ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ በርካታ ዜጎች ወደ ከተማ ግብርና ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በ2016 በጀት ዓመት በመዲናዋ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ሰዎች ቁጥር 723 ሺህ መድረሱን ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ ከ6 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በሰብል ምርቶች መሸፈኑን በመግለጽ ይህም ለዘርፉ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በከተማ ግብርና የተሰማራው አርሶ አደር ጌታነህ ተክለማርያም፤ በተሰማራበት የከተማ ግብርና ከራሱ አልፎ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት እያቀረበ መሆኑን ተናግሯል።

ሌላኛው አርሶ አደር ፍቅሬ ጫላ ባለው መሬት ላይ ተጠቅሞ በከተማ ግብርና ላይ በመሰማራት በምግብ ራሱን መቻሉን ገልጿል።


 

በተለይም በኮሚሽኑና በወረዳው በሚደረግላቸው የማዳበሪያና አረም የማጥፊያ መድሃኒት ድጋፍ ከበፊቱ የተሻለ ምርት እያገኙ መሆኑን አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል፡፡

በተለይም የሰብል ምርቶችን በክረምት ወቅት ዝናብን በመጠቀም ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን በመግለጽ፤ በጋም ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ያለውን የውሃ ችግር ኮሚሽኑ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነር ፋሩቅ ጀማል በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ አርሶ አደሮቹ በአካባቢያቸው ያለውን የውሃና ተያያዥ ችግሮች የከርሰ ምድር ውሃ በማውጣት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ማመቻቸቱን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የሙያዊ ስልጠና እና የግብዓት ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም