ህብረተሰቡ የስኳር ህመምን ለመከላከል ጤናማ የሆነ የኑሮ ዘይቤ ሊከተል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ የስኳር ህመምን ለመከላከል ጤናማ የሆነ የኑሮ ዘይቤ ሊከተል ይገባል
አዲስ አበባ፤ህዳር 2/2017(ኢዜአ)፦ህብረተሰቡ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የስኳር ሕመም ለመከላከል ጤናማ የኑሮ ዘይቤን ሊከተል እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የስኳር ህመምተኞች ማህበር ጋር በመሆን በየዓመቱ ህዳር 5 የሚከበረውን የስኳር ህመም ቀን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤በዓለም ላይ ከስኳር ህመም ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቁጥሩ እየጨመረ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከግማሽ ቢሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከስኳር ህመም ጋር አብሮ እንደሚኖሩና በኢትዮጵያም ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከስኳር ህመም ጋር እንደሚኖሩ ይገመታል ብለዋል።
በኢትዮጵያ አብዛኛው ሰው የስኳር ታማሚ መሆኑን አለማወቁ ትልቁ ችግር እንደሆነ ነው የጠቀሱት።
በመሆኑም ሰዎች ወደ ህክምና ተቋም ሄደው አስፈላጊውን የህክምና ምርመራ በማድረግ ራሳቸውን ሊያውቁ ይገባል ሲሉም አክለዋል።
የኢትዮጵያ የስኳር ህመምተኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ በበኩላቸው የስኳር ህመም የሚከሰተው ሰውነት አስፈላጊውን ስኳር በትክክል መጠቀም ሳይችል ሲቀር መሆኑን አንስተዋል።
የስኳር ህመም ታካሚዎች አስፈላጊውን ህክምና እና እንክብካቤ ካገኙ በተሟላ ጤንነት የመኖር እድል አላቸው ብለዋል።
በተጓዳኝም ከልክ ያለፈ ውፍረትን መቀነስ፤ ሲጋራ ማጨስ ማቆም፣ ለደም ግፊት የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን መቀነስ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
ኅብረተሰቡ ለስኳር በሽታ ተጋላጭ እንዳይሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ጎን ለጎንም የስኳር ሕሙማን አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አለም አቀፍ የስኳር ህመም ቀን "የስኳር ህመምና ሙሉዕ ደህንነት" በሚል መሪ ሃሳብ በአለም አቀፍ እና በኢትዮጵያ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ በመከበር ላይ ይገኛል።
አለም አቀፍ የስኳር ህመም ቀን ግንዛቤ የሚፈጥሩ ጋዜጠኞች ስልጠና መስጠት ፓናል ዲስኬሽንና ነፃ የምርመራ አገልግሎት እንዲሁም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ህዳር 5 እንደሚከበር ተገልጿል።