በጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኒሸቲቮች መንደሩን የቀየረው አርሶ አደር-አብነት ዴላሞ - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኒሸቲቮች መንደሩን የቀየረው አርሶ አደር-አብነት ዴላሞ
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኒሸቲቮች መንደሩን የቀየረው አርሶ አደር አብነት ዴላሞ
ለግብርና ካለው ፍቅር የተነሳ ራሱን ‘ወጣት አርሶ አደር አብነት’ ብሎ ይጠራል- አብነት ዴላሞ።
አብነት እርፍ የጨበጠው፣ ሞፈር ከቀንበር ያዋደደው፣ ከእርሻ የተዋወቀው በለጋነት ዕድሜው ነው።
ትምህርትና ስራን መሳ ለመሳ አጣጥሞ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ዘልቋል።
ዛፍ መትከል፣ ተፈጥሮን መንከባከብና በጽዱና ውብ አካባቢ የመኖር ውስጣዊ መሻት ነበረው።
በዚህም በከንባታ ዞን አዲሎ ዙሪያ ወረዳ በሞቃታማዋ ሀሚዶ ቀበሌ በሚገኘው የቤተሰቡ መሬት ላይ ለገጠር ኮሪደር አብነት የሆነ የገጠር መንደር መስርቷል።
"የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳቦች ውሰጣዊ መሻቴን ዕውን ለማድረግ አስችለውኛል" የሚለው አብነት፤ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የተጀመሩ ኢኒሸቲቮችን በመንደሩ በመተግበር ግንባር ቀደም ነው፡፡
ገጠሩን አዘምኖ የከተሜነትን የኑሮ ዘይቤ አላብሶታል፤ ሐሩሩን ወደ ገነት ለውጦታል።
ከግብርና ስራው ከሚያገኘው ገቢ በመጠቀም ከመኖሪያ ቤቱ ዙሪያ ገባውን ከ3 ሄክታር በላይ የሚሸፍን መሬትን በአረንጓዴ ስፍራ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ሸፍኗል።
አመሻሹን በአብነት አፀድ ውስጥ መዘዋወር መንፈስን የሚያድስ፤ ለዐይነ ህሊናም ሰላማዊ ስሜትን የሚፈጥር ነው።
የአብነት መንደር በባህላዊና ዘመናዊ ቤቶችን ያካተተ፣ በግዙፍ ሀገር በቀልና የውጭ ዛፎች የተሸፈነ፣ በፋውንቴን ያሸበረቀ፣ በጌጠኛ መተላለፊ መንገዶችና አበቦች የተዋበ እና በአዕዋፍት ዜማ የታጀበ በመሆኑ፤ ለእንግዶች ሎጅ ወይም የቱሪስት መዳረሻ መስሎ ግር ሊያሰኝ ይችላል።
"አንድ ገበሬ ጤናማና ጽዱ የኑሮ ዘይቤ መከተል ይችላል" የሚለው አብነት፤ “ቀን በስራ ስለፋ እውላለሁ፤ ማታ ከቤተሰቤ ጋር በመኖሪያ ቤቴ እዝናናለሁ ይላል፡፡
በገበታ ለሸገርና በገበታ ለሀገር የተገነቡ የቱሪስት መዳረሻዎች የራሱን የመኖሪያ አካባቢ እንዲለውጥ መነሳሳት እንደፈጠሩሉት ይናገራል።
‘ከተሰራ ሐሩሩን ወደ ገነት መለወጥ ይቻላል’ የሚለው አብነት፤ እርሱም አካባቢውን ወደ አረንጓዴ ገጽታ በመለወጥ ጽዱ የገጠር ኮሪደር ዕውን ማድረጉን ይናገራል።
በዚህ ስራውም ለሌሎች ተምሳሌት መሆን እንደሚፈልግ ነው የሚናገረው።
የኮሪደር ልማትን ሃሳብ ላመነጩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያን ለመለወጥ እየሰሩት ባለው ታላቅ ስራም በግቢው ውስጥ በስማቸው ፓርክ መሰየሙን ይገልጻል።
አብነት የቤተሰቡን የእርሻ ማሳ በመኸርና በበጋ መስኖ በማልማት የምግብ ሉዓላዊነት ለማስፈን ይተጋል።
ዘመናዊ የዶሮ እርባታ፣ የዘመናዊና ባህላዊ የንብ ማነብ፣ የወተት ላሞች እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ልማት የአብነት መንደር ተጨማሪ ምልክቶች ናቸው፡፡
በዚህም በደጅ አረንጓዴ ውበት የተጎናጸፈ፤ ሌማቱም የተትረፈረፈ ነው፡፡
ከቤተሰቡም አልፎ ለአካባቢው ማህበረሰብም በማሳየትም መንግስት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚለውን ንቅናቄ በቀዳሚነት በመተግበር እየሰራ መሆኑን ይናገራል።
ከጥቂት ዓመታት ውስጥ በረሃውን ወደ ገነት መለወጥ ችያለሁ የሚለው አብነት፤ በቁርጠኝነት ከተሰራ ድህነትን ማሸነፍ፣ የኑሮ ዘይቤንና ሀገር መለወጥ ይቻላል ይላል፡፡
በሌላ በኩል ሶስት የኤሌክትሪክ ወፍጮዎች በመትከል እና ኤሌክትሪክ መብራት በማስገባት ለመንደሩ ጎረቤቶች በቀላሉ አገልግሎት እየሰጠም ይገኛል፡፡
የጉድጓድ ውሃ በመቆፈርም የአካባቢው ወጣቶች አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያለሙ ይደግፋል።
በተጨማሪም የአካባቢው ነዋሪዎችን በማህበር በመዳረጃት የክላስተር ግብርና እንዲሰፋ እየሰራ ሲሆን፤ይህን በማስፋትም ከራስ ባለፈ ለሀገር የሚተርፍ ምርት ለማምረት ውጥን ይዟል፡፡
የአብነት አብነታዊ ጉዞ ግን ይህ ብቻ አይደለም።
ከማሳው ውስጥ ሁለት ሄክታር መሬት ለግብርና ምርምር እንዲውል ለክልሉ ግብርና ቢሮ በስጦታ ማበርከቱንም ነው የሚናገረው፡፡
በስፍራው ምርምር ማድረግ ለሚፈልጉ የሀገር ውስጥና የውጭ ተመራማሪዎች ማረፊያ ቤትም ገንብቷል።
የሀሚዶ አካባቢ ለም መሬት እና አምራች አካባቢ ቢሆንም ግብርናው ባለመዘመኑ፣ የማህበረሰቡ ግንዛቤም ባለማደጉ ወጣቶች ለስደት ሲዳረጉ መቆየታቸውን ያነሳል።
የእርሱና መሰሎቹ ተሞክሮ ግን ወጣቶች ከስደት ይልቅ ወደ ቀያቸው ተመልሰው ከራሳቸው አልፈው ለሀገር የተረፈ ምርት እንዲያቀርቡ ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ያምናል።
በቀጣይ የየትኛውም የዓለም ክፍል የሚመጡ ጎብኚዎች የኢትዮጵያ አርሶ አደር ቤት መልክ ምን እንደሚመስል የሚያስቃኝ የቱሪስት መዳረሻ በመንደሩ ውስጥ የመገንባት ዕቅድ ይዟል።
ከአብነት ጎረቤቶች መካከል ወጣት አምሳሉ አህመድና አቶ አህመድ ዋይጀጎ፤ አብነት ለቀዬው ማህበረሰብ መለወጥ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰርቶ ከማሳየቱ ባሻገር ለስራዎቻቸው መቃናትም ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ይናገራሉ።
የአብነት መንደር ተሞክሮ ኢትዮጵያ በብርቱ ልጆቿ ጥረት ወደ ተሻለ ምዕራፍ መቀየሯ አይቀሬ መሆኑን በግልጽ የሚያመላክት ነው፡፡፡