ቀጥታ፡

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚና  የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በትብብር  ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት  በአመራር ልማት ላይ በትብብር  ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ ፈርመዋል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤  ስምምነቱ በአገሪቱ የፖለቲካ ባሕልን ለመቀየርና ዘመናዊ አካሔድን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው።

በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችን አቅም ለማሳደግ ከአካዳሚው ጋር በጋራ ለመስራት መወሰኑን ጠቅሰዋል።

በምክር ቤቱ ስር ከ60 በላይ አገራዊና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመዘገቡ ሲሆን፤ ስምምነቱ በሰው ኃይል ልማት ዘርፍ በቅንጅት ለመስራት እንደሚረዳም አመልክተዋል።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው፤ አካዳሚው በአገሪቱ የአመራር ልማት ስራ ላይ ሪፎርም ቀርጾ እየሰራ ነው ብለዋል።

ከዚህ ውስጥም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት መስራት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም