ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በአዘርባጃን መካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በአዘርባጃን መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ህዳር 2/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት ዓለም አቀፉ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 29) በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ፣ለአየር ንብረት ለውጥ የፋይናንስ አቅምን ማጠናከር ብሎም ዘላቂነት ያለው የአየር ንብረት ለውጥን ማረጋገጥ ላይ እንደሚያተኩር ይጠበቃል።
የዘንድሮው የኮፕ 29 ጉባኤ ''በጋራ ለአረንጓዴ ምድር'' በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ እየተሳተፈች ሲሆን በአየር ንብረት ጥበቃ ላይ ለምታደርገው አበርክቶት ድጋፍ እና አጋር ለማግኘት ትጠቀምበታለች ተብሎም ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ኢኒሼቲቭ በተለይ በግብርና፣በኢኮቱሪዝም እና በታዳሽ ሀይል ላይ እየተሰራ ያለው ስራ ዘላቂ የሆነ አየር ንብረትን ለማስጠበቅ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑ ይታወሳል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የተራቆተ መሬት የደን ሽፋንን መልሶ ለማልማት ያደረገችው ቁርጠኝነት እና ዘላቂነት ያለው የመሬት አጠቃቀም በጉባኤው ላይ በተሞክሮነት ይቀርባል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ ልዑክ በታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያግዝ ድጋፍ እንዲደረግ ትኩረት ያደርጋል ተብሏል።
የሃይል አቅርቦት ምንጭ፣የሰብአዊ ልማት፣የምግብ ዋስትና እና ብዝሃ ህይወት ላይ ትኩረት ያደረጉ አጀንዳዎች ናቸው ተብሏል።
በተጨማሪም በጉባኤው የአየር ንብረት ፋይናስን ማጠናከር፣ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ማስቻል እና ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰብ ተግባራዊ የሆነ ድጋፍ ማድረግ የሚለው ይገኝበታል።
ይህም ውሳኔ በቀጣይ ለሁሉም ዘላቂ እና የተሻለች ዓለምን ለጋራ ለማቆየት ያስችላል ነው የተባለው።
ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት በሚደረገው ጉባኤው ላይ ከ198 አባል ሀገራት የተውጣጡ የሀገራት መሪዎች እና ከፍተኛ ባለ ስልጣናት በጉባኤው ይሳተፋሉ።
ባለፈው አመት በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የተደረገው ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 28) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተገኙ ሲሆን ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ መሻሻል በርካታ ውሳኔዎች መተላለፋቸው ይታወሳል።
የዘንድሮው ጉባኤም ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።