ቀጥታ፡

የቤኑና መንደር ለኢትዮጵያ ቱሪዝም መነቃቃት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ማራኪ ስፍራ ነው - መርየም ሳሊም

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2017(ኢዜአ)፦ የቤኑና መንደር ለኢትዮጵያ ቱሪዝም መነቃቃት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ማራኪ ስፍራ መሆኑን በዓለም ባንክ የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ፣ የደቡብ ሱዳን እና የሱዳን ዋና ዳይሬክተር መርየም ሳሊም ገለጹ።

ቤኑና መንደር በበሰቃ ሃይቅ ዳርቻ እጅግ ዘመናዊ መኝታ ክፍሎች፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ ሲኒማ ቤት፣ መዝናኛ ስፍራ፣ ስፓ እንዲሁም የፍራፍሬ ልማት እና የሌማት ትሩፋትን አካቶ በመያዝ ለምርቃት በቅቷል።

የመንደሩ ግንባታም ባህላዊ የኪነ-ህንጻ ጥበብን ከዘመናዊ ግንባታ ጋር አቀናጅቶ በመያዝ ለአካባቢው ማህበረሰብ የመስህብ ልማት ተጨማሪ የቱሪዝም አቅም የፈጠረ መዳረሻ ስፍራ ሆኗል።


 

በዚሁ ጊዜ በዓለም ባንክ የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ፣ የደቡብ ሱዳን እና የሱዳን ዋና ዳይሬክተር መርየም ሳሊም፤ የቤኑና መንደር አስደናቂ የቱሪስት መስህብ ስፍራ ነው ብለዋል።

በቤኑና መንደር ግንባታና የአካባቢው ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ትልቅ የሃብት አቅም መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው የተፈጠረውን የደስታ ምንጭነት ለመጋራትም በቀጣይ ከቤተሰባቸው ጋር በመሆን በአካባቢው ለመዝናናት እንደሚመጡ ገልጸዋል።

በቤኑና መንደር ልማቱ የተሰናሰለበት መንገድም ዘና ማለትን ለሚሹ ሰዎች ምቹ አጋጣሚን የፈጠረ ማራኪ ስፍራ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም አካባቢው ለእርሻ፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ የግብርና ምርታማነት ምቹ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

 

በዚህም የዜጎችን የገቢ ምንጭ በማስፋት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚበጁ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የቤኑና መንደርም ለቱሪዝም መስህብነት ትልቅ አቅም በመፍጠር ታሪካዊ ስራ የተሰራበት አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል።

በመንደሩ የብርቱካን፣ ሎሚ፣ ፓፓዬና ማንጎ ልማት እንዲሁም ዶሮ፣ ግመል፣ የከብትና ፍየል እርባታ ስራን አሰናስሎ በመያዝ ከመዝናኛ ስፍራነት ባሻገር በፍራፍሬና ሌማት ትሩፋት ልማትን በማስተሳሰር ትምህርት የሚወሰድበት ስለመሆኑ ተገልጿል።

የቤኑና መንደር ግንባታም በኢትዮጵያ መንግስት፣ በግሉ ዘርፍና በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግስት ትብብር የተገነባ ሲሆን ስካይ ላይት ሆቴል ደግሞ የማስተዳደር ስራን የሚያከናውን መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም