ኢትዮ ቴሌኮም እና የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ስማርት ቢሾፍቱ ፕሮጀክትን ዕውን ማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ቴሌኮም እና የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ስማርት ቢሾፍቱ ፕሮጀክትን ዕውን ማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮ ቴሌኮም እና የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ስማርት ቢሾፍቱ ፕሮጀክትን ዕውን ማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዓለማየሁ አሰፋ ፈርመውታል።
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ስማርት ቢሾፍቱ ፕሮጀክት የክላውድ፣ ጥሪ ማዕከል፣ ዳታ ሴንተር፣ ፍጥነት እና ጥራት ያለው ኢንተርኔት፣ የኦፕቲካል ፋይበር እና ሌሎች የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ከተማዋን የሚያዘምን ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የመዘጋጃ አገልግሎቶችን ጨምሮ ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ ትራንስፖርት እና የግብር አሰባሰብ የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ለማዘመን እንዲሁም አስተማማኝ ደህንነት ያላት ቢሾፍቱን ዕውን ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሁሉን አቀፍ የዲጂታል መፍትሄዎች ተጠቃሚነትን ከማሳደግ ባሻገር ክፍያዎችን በቴሌብር በቀላሉ በማስፈጸም ውጤታማነትን ለማሳደግ እንደሚረዳም እንዲሁ።
በተለይም ከተማዋን ለቱሪዝም መዳረሻነት፣ ለኢንዱስትሪ እና ለኢንቨስትመንት ያላትን ተመራጭነት በማሳደግ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዓለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው ስምምነቱ ያለንን ጸጋ በአግባቡ በማወቅ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚረዳ ነው ብለዋል።
የክፍያ ስርዓቱን፣ የትራንስፖርት፣ የጤና፣ የትምህርት በአጠቃላይ አገልግሎቶችን ለማዘመን ያግዛል ነው ያሉት፡፡