ቀጥታ፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፍትህ አገልግሎትን ቀልጣፋ፣ ፍትሀዊና ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው

ቦንጋ፤ ህዳር 02/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፍትህ አገልግሎትን ቀልጣፋ፣ ፍትሀዊና ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ ገለጹ።

የፍትህ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባር እንዲሁም በባህላዊ ዳኝነት ሥርዓት ዙሪያ የሚመክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ እንዳሉት፣ የፍትህ አገልግሎትን ቀልጣፋ፣ ፍትሀዊና ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዙ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

ከዚህ ውስጥ አንዱ የፍትህ ትራንስፎርሜሽንን በተቀናጀና በተናበበ አግባብ መተግበር መሆኑን ገልጸው ይህም ህዝቡ ቀልጣፋና ጥራት ያለው የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

 

ትራንስፎርሜሽኑ በፍትህ ተቋማት የሚታዩ የአደረጃጀት፣ የአሠራር እንዲሁም የሰው ኃይል እጥረትና ሌሎች ማነቆዎችን ለመፍታት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

የፍትህ ዘርፉ መዘመን ለዲሞክራሲያዊ ባህል መጎልበት፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈን፣ ሠላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥና የልማት ግቦችን ለማሳካት ከፍተኛ ጠቀሜት እንዳለውም አክለዋል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ እሼቱ ጎዴቶ በበኩላቸው የፍትህ ዘርፉን ቀልጣፋ፣ ፍትሀዊና ውጤታማ ለማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ መሆኑን አስታውስዋል።


 

በክልሉ የፍትህ ተቋማት የተካተቱበት የሶስት ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ መሆኑንም አስረድተዋል።

ለዚህም የክልሉ ፍትህ ቢሮ ዝርዝር ተግባራት ያሉት የሶስት ዓመት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የድርጊት መርሃ ግብር ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

በመድረኩ ላይ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ መቱ አኩን ጨምሮ የክልልና የዞን ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም