ቀጥታ፡

ተቋማቱ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2017(ኢዜአ)፦ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የአዲስ አበባ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ እና የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ እንዲሁም ብሄራዊ መታወቂያ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

የስምምነቱ ዓላማ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ለሲቪል ምዝገባ እና ለወሳኝ ኩነት የቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን ለማልማት፣ ለማማከር፣ ለመተግበር፣ በቀጣይነት ክትትል ለማድረግና በትብብር ለመስራት ያለመ መሆኑ ተጠቅሷል።

እነዚህ አገልግሎቶች ከዲጂታል መታወቂያ ጋር የተሳሰሩ እንደሚሆኑ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በስምምነቱ ወቅት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ እንደተናገሩት የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ከዚህ ቀደም የነበሩ ክፍተቶችን በመቅረፍ እና አሰራሩን አውቶሜት ለማድረግ ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኤጀንሲውን አሰራር ዲጂታላይዝ በማድረግ ሂደት ላይ ለመደገፍና በማማከር ሰፊ ስራዎችን እንደሚስራ ገልጸዋል።


 

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) በበኩላቸው አዲስ የሚገነባው የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ስርዓት ከተማዋን ስማርት ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግረዋል

በተጨማሪም በከተማዋ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከልና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማስተሳሰር ስምምነቱ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዮናስ አለማየሁ በበኩላቸው ኤጀንሲው በዋናነት የሚያከናውናቸው ተግባራት የወሳኝ ኩነት እና የነዋሪነት መታወቂያ ምዝገባ አገልግሎት መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁንና ቀደም ባለው ጊዜ የነበረው አሰራር ዘመኑን የዋጀ ባለመሆኑና የተገልጋዮችን ፍላጎት የሚያሟላ ባለመሆኑ ቴክኖሎጂ መጠቀም የግድ ማለቱን ገልጸው ከተቋማቱ ጋር በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰለሞን አማረ በበኩላቸው ከሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር በጋራ በመስራት አመርቂ ውጤት እንደሚገኝ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

የብሄራዊ መታወቂያ ስራ አስኪያጅ አቶ ዮዳሄ አርአያስላሴ በበኩላቸው ተፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት መሰል ቅንጅታዊ አሰራሮችና ትብብሮች ወሳኝ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም