ቀጥታ፡

ከ294 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ከ294 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን አስታወቀ፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙት ከጥቅምት 22 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ባደረገው ክትትል መሆኑንም ገልጿል፡፡

በዚህም 279 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የገቢ እና 14 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የወጭ ኮንትሮባንድ እቃዎች፤ በድምሩ 294 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን ነው ያስታወቀው፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የግንባታ እቃዎች፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደገኛ እጾች፣ መድኃኒት፣ የምግብ ዘይት፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች እና የውጭ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ብሏል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ እና በበረራ የተያዙ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 14 ተጠርጣሪዎች እና 7 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ የተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞችንና አመራሮችን፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላትን እንዲሁም ህዝቡን አመስግኗል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ህገ-ወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ኮሚሽኑ ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም