ቀጥታ፡

በተጠባቂው የለንደን ደርቢ ጨዋታ ቼልሲ እና አርሰናል ነጥብ ተጋርተዋል 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 1/2017 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የለንደን ተቀናቃኞቹ ቼልሲ እና አርሰናል አንድ አቻ ተለያይተዋል።

በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የ23 ዓመቱ ብራዚላዊው የክንፍ መስመር ተጫዋች ጋብርኤል ማርቲኔሊ በ60ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ አርሰናልን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር።

ይሁንና በ70ኛው ደቂቃ የ24 ዓመቱ ፖርቹጋላዊው የክንፍ ተጫዋች ፔድሮ ኔቶ ከመረብ ጋር ያገናኛት ግብ ቼልሲን አቻ አድርጋለች።

ውጤቱን ተከትሎ ቼልሲ እና አርሰናል በተመሳሳይ 19 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።

አርሰናል የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ዛሬ በተደረጉ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ ሌይስተር ሲቲን 3 ለ 0 እንዲሁም ኒውካስትል ዩናይትድ ኖቲንግሃም ፎረስትን 3 ለ 1 አሸንፈዋል።

አዲስ አዳጊው ኤፕስዊች ታውን ከሜዳው ውጪ ቶተንሃም ሆትስፐርስን 2 ለ 1 ረቷል።

ሊቨርፑል ሊጉን በ28 ነጥብ ሲመራ ማንችስተር ሲቲ በ23 ነጥብ ይከተላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም