ቀጥታ፡

15ኛው የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና የሚኒስትሮች ጉባኤ በአህጉሪቱ የንግድ ጉዳዮች ላይ ስኬታማ እና ፍሬያማ ውይይቶች የተካሄደበት ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2017(ኢዜአ)፦ 15ኛው የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና የሚኒስትሮች ጉባኤ በአህጉሪቱ የንግድ ጉዳዮች ስኬታማ እና ፍሬያማ ውይይቶች የተካሄደበት እንደነበር የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለፁ።

15ኛውን የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና የሚኒስትሮች ጉባኤ ለመታደም የመጡ ሚኒስትሮች በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሚገኘውን የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ማሳያ ማዕከል እና በገላን የሚገኘውን ኤኤምጂ የቡናና የብረታብረት ፋብሪካ ጎብኝተዋል።


 

በዚሁ ወቅት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የወጪ ንግድ አቅም ለጎብኚዎቹ አስረድተዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ 15ኛውን የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና የሚኒስትሮች ጉባኤ በአፍሪካ ንግድ ጉዳዮች ዙሪያ ስኬታማ እና ፍሬያማ ውይይቶች የተካሄደበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ ሀገራት የንግድ ልውውጥና የእሴት ሰንሰለት ልማትን በሁሉም ዘርፎች ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉንም አንስተዋል።

በአህጉሪቱ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ በቅርቡ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና የሙከራ ትግበራ ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቋን እንደገለጸችም ተናግረዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ፅህፈት ቤት ዋና ጸሀፊ ዋምኬሌ ሜኔ እና የታንዛኒያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሰሌማኒ ጃፎ በጉብኝቱ በተመለከቱት ስኬት መገረማቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልምድና ተሞክሮ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም