ቀጥታ፡

የትብብር መድረኩ የእርስ በርስ ግንኙነትን በማጠናከር የመሰረተ ልማት ስራዎችን ለማስፋፋት ዕድል እየፈጠረ ነው

ሀዋሳ፤ ህዳር 1/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ የከተሞችን የእርስ በርስ ግንኙነት በማጠናከር የመሰረተ ልማት ስራዎችን ማስፋፋት የሚያስችል ዕድል እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የከተማ ከንቲባዎች በበኩላቸው ከትብብር መድረኩ የሚገኙ ተሞክሮዎችን ወደ አካባቢያቸው በማስፋት እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዱአለም ጤናው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መድረኩ ከተሞች እርስ በርስ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ በማመቻቸት የበኩሉን እየተወጣ ነው፡፡


 

የትብብር መድረኩ በከተሞች ለሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች ውጤታማነት የአመራሩን አቅም የማጎልበትና በልምድ ልውውጡ መልካም ተሞክሮን ማስፋት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በበርካታ ከተሞች ላይ ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸው የትብብር መድረኩ በሃገሪቱ ያሉ የልማት ስራዎችን የሚደግፉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

የአመራር አቅም መገንባት፣ የመልካም አስተዳደር ስራዎችን የሚደግፉ ፕሮጀክቶችን መቅረጽና የማዘጋጃ ቤቶችን አሰራር በማዘመን የገቢ አቅማቸውን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በይርጋለምና ቡልቡላ ከተማ ማዘጋጃ ቤቶች የገቢ አሰባሰቡን ማዘመን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመዘርጋትና የባለሙያውን አቅም ማሳደግ የሚያስችለው የሙከራ ፕሮጀክት ገቢን በማሳደግ ጉልህ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል፡፡

በከተማና መሰረተ ልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አፈጻጸም ውጤታማነት የአመራሩን ሚና ለማጠናከር የትብብር መድረኩ የአመራሩን አቅም የማጎልበት ተግባር ደግሞ ሌላው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመትም 20 የሚሆኑ ከተሞችን ማህበራዊ መስተጋብርና ኢኮኖሚያዊ መሰረት ላይ ያተኮረ ጥናት ማስጠናታቸውንም ተናግረዋል፡፡


 

በጥናቱ የተሳተፉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልማት ጥናት ኮሌጅ መምህር መሳይ ሙሉጌታ(ዶ/ር) የትብብር መድረኩ ያስጠናው ጥናት በከተሞች መካከል ጤናማ የሆነ ውድድር እንዲፈጠርና የልምድ ልውውጥ እንዲጠናከር የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

የጥናቱ ውጤት በአብዛኞቹ ከተሞች የመረጃ አያያዝ ክፍተት መኖሩን ያመላከተ በመሆኑ የመረጃ አያያዝ ስርዓቱን ለማዘመን መስራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ ሳይመን ሙን(ዶ/ር) በበኩላቸው የትብብር መድረኩ በመሰረተ ልማት ወደ ኋላ ለቀሩ ከተሞች የበለጠ አቅም የሚፈጥር በመሆኑ በርካታ ልምዶችን አግኝተናል ብለዋል፡፡


 

የጋምቤላ ከተማ የትብብር መድረኩ ያስጠናው ጥናት አካል መሆኑን ጠቅሰው በመረጃ አያያዝ ረገድ ያሉባቸውን ክፍተቶች ለመቅረፍ እንደሚሰሩና ከሌሎች ከተሞች የተገኙ ልምዶችን በመውሰድ መሰረተ ልማቱን ማስፋፋት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የትብብር መድረኩ በከተሞች መካከል የልምድ ልውውጥ በመፍጠር መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋት የሚያግዝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፍሬው ሞገስ(ዶ/ር) ናቸው፡፡


 

የትብብር መድረኩ ጥናት መሰረት በተለይ በከተሞች ያለውን የመረጃ አያያዝ ክፍተት ለማረም የሚያስችል ስራ በትኩረት እንደሚያከናወኑ ጠቅሰው መድረኩ ክፍተቶቻችንን እንድናይም የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ደኤታና ከ100 የሚበልጡ የከተማ ከንቲባዎችና የከተማ አመራሮች በተገኙበት በሃዋሳ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም