የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከለውጡ በኋላ ያደረገው ሪፎርም በታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተመራጭ አድርጎታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከለውጡ በኋላ ያደረገው ሪፎርም በታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተመራጭ አድርጎታል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከለውጡ በኋላ ያደረገው ሪፎርም በታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተመራጭ እንዳደረገው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም የማጠቃለያ እና የምስጋና መርሀ ግብር "በተለወጠ ሀገር ለላቀ አገልግሎት እየተጋ ያለ ፖሊስ" በሚል መሪ ሃሳብ አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በማጠቃለያ መርሀ ግብሩ ወቅት የኢትዮጵያ ፖሊስ ሆስፒታልን እድሳትና የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ከ116 ዓመት በላይ ያስቆጠረ አንጋፋ ተቋም ነው።
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከለውጡ በኋላ በተደረገ ስር ነቀል ሪፎርም የፖሊስ ሰራዊቱን ግዳጅ የመፈጸምና ተልዕኮ የመወጣት አቅም የሚያሳድግ የተደራጀ ተቋማዊ አሰራር ተፈጥሯል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ሆስፒታል እና የሀረር ፖሊስ ሆስፒታል ከለውጡ በኋላ የተደራጀ የህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው የተደረገው ሪፎርም ውጤታማ ለመሆኑ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቅርቡ የፎረንሲክ ማዕከሉ ተጠናቆ ይመረቃል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ፤ ሪፎርሙ ቀልጣፋ የወንጀል ምርመራ ስርዓት ለመዘርጋት ማስቻሉን አንስተዋል።
በአጠቃላይ በወንጀል መከላከልና በወንጀል ምርመራ ዘርፍ በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ ማከናወኑ በታላላቅ አለም አቀፍ ተቋማት ተመራጭ ለመሆን አስችሎታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ነብዩ ዳኜ በበኩላቸው ከለውጡ በኋላ በተቋሙ በሁሉም ዘርፎች መጠነ ሰፊ ሪፎርም መደረጉን አንስተዋል።
በዚህም የዜጎችን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ የሚችል ሠራዊት ተፈጥሯል ብለዋል።
ከውጭ እና ከውስጥ የተጠናከረ ትብብር በመፍጠር የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ማስከበር የሚያስችል አቅም ተገንብቷል ነው ያሉት።
በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር ወንጀልን በጋራ መከላከል የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ገልጸዋል።