ዓይን ላይ የደረሰ ጉዳትን በጊዜው በመታከም የዓይን ህመምን ሳይባባስ መከላከል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዓይን ላይ የደረሰ ጉዳትን በጊዜው በመታከም የዓይን ህመምን ሳይባባስ መከላከል ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2017(ኢዜአ)፦ ዓይን ላይ የሚደርስ ጉዳትን በጊዜው በመታከም የዓይን ብሌን ጠባሳ ህመም ሳይባባስ መከላከል እንደሚቻል የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው ወጣቶች ገለጹ።
ወጣት ወጋየሁ ፈጠነ ትውልድና እድገቱ ምዕራብ ሀረርጌ እንጨር ወረዳ ነው።
ቤተሰቦቹም እድሜው ሲደርስ እንደማንኛውም ልጅ የነገ ብሩህ ተስፋውን በትምህርት ዓለም እውን እንዲያደርግ ተስፋ ሰንቀው ወደ ትምህርት ቤት ለማስገባት ቢሞክሩም አለመቻላቸውን ይገልጻል።
በአይኖቹ ላይ ያጋጠመው የዓይን ብሌን ጠባሳ ለትምህርቱ መሰናከል ምክንያት መሆኑን በመናገር የህመሙ መንስኤ ደግሞ በህፃንነቱ ያጋጠመው የኩፍኝ በሽታ መሆኑን ያስታውሳል።
በህፃንነቱ የኩፍኝ በሽታውን ለመከላከል ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ወይም ክትባት ማግኘት ባለመቻሉ የዓይን ብሌን ጠባሳ ተጋላጭ መሆኑን ተናግሯል።
ባጋጠመው የዓይን ብሌን ጠባሳ ህመም እንደእኩዮቹ ትምህርት መማር አለመቻሉ ከፍተኛ ቁጭት ላይ ጥሎት እንደነበር ወደ ኋላ መለስ ብሎ ያስታውሳል።
ነገር ግን ለመዳን ካለው ጉጉት የተነሳ ተስፋ ባለመቁረጥ ወደ ተለያዪ ህክምና ተቋማት በመሄድ ህክምና ለማግኘት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሷል፡፡
የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ የተደረገለት በባሌ ዞን ተወልዶ ያደገው ወጣት ፍሬው ሺበሺ በበኩሉ የህመሙ መነሻ ከ12 ዓመት በፊት ሞተር ቢስኪሌት ሲነዳ መሬት ላይ በወደቀበት አጋጣሚ እንጨት የግራ ዓይኑን ስለወጋው እንደሆነ ተናግሯል።
ከአደጋው በኋላ ቶሎ ህክምና ለመሄድ አለመሞከሩን በመናገር ይህም በህይወቱ ትልቅ ዋጋ እንዳስከፈለው ገልጿል።
ወጣት ወጋየሁ በ2ሺ ዓ.ም አካባቢ በዳግማዊ ሚኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል ምርመራ አድርጎ የግራ እና የቀኝ ዓይኑ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ እንደሚያስፈልገው ተገልፆለት ህክምና መጀመሩን አውስቷል።
የመጀመሪያውን የግራ ዓይኑን የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ በ2 ሺ ዓም ከወሰደ በኋላ 2002 ዓ.ም ህልሙን እውን ለማድረግ ትምህርት መጀመሩ ከምንም በላይ እንዳስደሰተው በማስታወስ በአሁኑ ሰዓት በኪዊንስ ኮሌጅ የ2ኛ ዓመት የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ተማሪ እንደሆነም ጠቁሟል።
በተመሳሳይ ወጣት ፍሬው የግራ ዓይኑ የብሌን ንቅለ ተከላ ከተደረገለት አራት አመታት እንዳስቆጠረ እና በየጊዜው ተገቢውን የህክምና ክትትል እያደረገ መሆኑን ተናግሯል።
ሰዎች ዓይናቸው ላይ ጉዳት ሲደርስበቸው ችላ ብሎ ከማለፍ ይልቅ በወቅቱ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ምርመራ እንዲያደርጉም መክሯል።
በኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት የዓይን ባንክ ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አምሳለ ጌታቸው በርካታ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ገልፀዋል።
የዓይን ብሌን ጠባሳ በሰዎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም አገልግሎቱ የዓይን ብሌን ለመሰብሰብ የማህበረሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።