በአማራ ክልል በሚገኙ የጤና ተቋማት የላቦራቶሪ አገልግሎትን የማዳረሱ ተግባር ላይ መረባረብ እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በሚገኙ የጤና ተቋማት የላቦራቶሪ አገልግሎትን የማዳረሱ ተግባር ላይ መረባረብ እንደሚገባ ተመለከተ
ባህርዳር፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በሚገኙ ጤና ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ የላቦራቶሪ አገልግሎትን የማዳረሱ ተግባር ላይ በቅንጅት መረባረብ እንደሚገባ ተመለከተ።
"የላቦራቶሪ አገልግሎት ለማይበገር የጤና ስርዓት’’ በሚል መሪ ሃሳብ 3ኛው ክልል አቀፍ የላቦራቶሪ ፌስቲቫል በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።
በፌስቲቫሉ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ በክልሉ ሁሉም የጤና ተቋማት ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል።
ለዚህም የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሁናዊ ሁኔታውን ግምት ውስጥ በማስገባት ቀጣይነት ያለው የጤና ላቦራቶሪ አገልግሎት ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የክልሉን አሁናዊ ሁኔታ በአግባቡ በመረዳት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለጤናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥተው በቅንጅትና በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ ጌትነት በበኩላቸው፤ ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መንስኤ ማረጋገጥ የሚቻለው ጥራት ያለው የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ሲቻል እንደሆነ አመልክተዋል።
ለዚህም በሽታን በተገቢው መንገድ ለመለየትም ሆነ ትክክለኛውን ህክምናና መድኃኒት ለመስጠት ጥራቱን የጠበቀ የላቦራቶሪ አገልግሎት በጤና ተቋማት ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
"በሽታን ለመለየትና ጥራት ያለው የጤና ሽፋንን በክልሉ ለማረጋገጥ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ እየሰራ ነው" ያሉት ደግሞ የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ናቸው።
ላቦራቶሪዎች ተላላፊ በሽታዎችን በመመርመርና በማከም ሁለንተናዊ የጤና አገልግሎት ሽፋንን ለማረጋገጥ ሁነኛ መሳሪያዎች እንደሆኑም ገልጸዋል።
የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው፤ ለጤናው ዘርፍ መዘመን ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎት በሁሉም ጤና ተቋማት ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
የላቦራቶሪ አገልግሎት ግብዓት በማሟላትና ጥራቱን በመጠበቅ እንዲሁም ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ህክምና ላቦራቶሪ ማህበር ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር አስቴር ፀጋዬ እንዳሉት፤ ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ተገቢ ነው።
ለዚህም ሁሉም ባለሙያዎች ጥራት ያለው አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በፌስቲቫሉ የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች፣ የጤና ተቋማት፣ የዩኒቨርሲቲና ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማትና ግለሰቦች ዕውቅና ተሰጥቷል።