በስልጠናው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስከበር የሚያስችል እውቀትና ወታደራዊ ጥበብ አግኝተናል - ተመራቂ ወታደራዊ መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
በስልጠናው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስከበር የሚያስችል እውቀትና ወታደራዊ ጥበብ አግኝተናል - ተመራቂ ወታደራዊ መኮንኖች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፦ በስልጠናው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስከበር የሚያስችል እውቀትና ወታደራዊ ጥበብ ማግኘታቸውን የወልወል ድህረ-ምረቃ እና የ25ኛ ሰላም ኮርስ ተመራቂ መኮንኖች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚና የሁርሶ ዕጩ መኮንን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የወልወል ድህረ-ምረቃ እና የ25ኛ ሰላም ኮርስ ዕጩ መኮንኖችን አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ ጄኔራል መኮንኖችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ተመራቂ ዕጩ መኮንኖች በማሠልጠኛ ማዕከሉ ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የቆዩና የሚጠበቅባቸውን ሥልጠና ወሥደው ያጠናቀቁ ናቸው።
ተመራቂዎች በእውቀት፣ በክህሎትና በአስተሳሰብ ሙሉ የሚያደርጋቸውን የመሪነት ስልጠና መውሰዳቸውንም ገልጸዋል።
ምክትል መቶ አለቃ ፍራኦል አዱኛ በሰጠው አስተያየት፤ እንደ ቀደመው ጊዜ ሁሉ ሀገሩን ይበልጥ ማገልገል የሚችልበትን ዕውቀት እና ወታደራዊ ጥበብ ማግኘቱን ተናግሯል።
የአመራርነት ሚናውን በብቃት ለመወጣት መዘጋጀቱን ገልጾ፤ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆኑንም ጠቁሟል።
ምክትል መቶ አለቃ ምትኩ በየነ ሀገርና ህዝብ የጣሉበትን አደራ በሚገባ መወጣት የሚያስችል ስልጠና ማግኘቱን ገልጾ፤ ለዚህም መዘጋጀቱን ተናግሯል።
ከስልጠናው ያገኘውን እውቀትና ወታደራዊ ጥበብ በአግባቡ በመተግበር ለብሔራዊ ጥቅም መረጋገጥ እንደሚተጋም ጠቁሟል።
ምክትል መቶ አለቃ ቃልኪዳን ደሴ እና ምክትል መቶ አለቃ ፍራኦል አዱኛ የኢትዮጵያን ሰላም እና አንድነት ለማረጋገጥ እንደሚተጉ ገልጸዋል።