ቀጥታ፡

ፖሊስ ሕዝቡን በማሳተፍ የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት በዘላቂነት የማስጠበቅ ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ፖሊስ  ዘመኑ የሚጠይቀውን አሰራር በመከተልና ሕዝቡን በማሳተፍ  የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት በዘላቂነት የማስጠበቅ ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ በ2016 በጀት ዓመት የላቀ የሥራ አፈፃፀም ላሳዩ  የፖሊስ አመራሮች፣ አባላትና ተቋሙ ስኬታማ ተግባር እንዲያከናውን ድጋፍ ላደረጉ አካላት እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል።  


 

በእውቅናና ሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋውና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የመዲናዋና የፌደራል  ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።  

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፣ በሪፎርሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ በብቁ የሰው ኃይል እንዲደራጅና ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ ተላብሶ እንዲሰራ ተደርጓል። 

የመዲናዋ ፖሊስ በሥልጠና አቅሙን በማሳደግ ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ተላብሶ እንዲሰራ፣ ተደራሽነቱን እንዲያሰፋ እንዲሁም አሰራሩን እንዲያዘምን ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም የአዲስ አበባ ፖሊስ የመዲናዋን ሕዝብ እንቅስቃሴ ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆን ተልእኮውን በትጋትና በብቃት እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል።  

ፖሊስ በ2016 በጀት ዓመት ሰላምና ደኅንነት ለማወክ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ መዲናዋን የልማትና የሰላም ተምሳሌት እንድትሆን አድርጓል ብለዋል። 

የአዳስ አበባ ፖሊስ ወንጀልን ቀድሞ የመከላከልና የሕግ የበላይነትን የማስከበር አቅሙ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ኅብረተሰቡን በማሳተፍና ዘመኑ የሚጠይቀውን አገልግሎት በማሳደግ ሰላምና ደኅንነት የመጠበቅ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።  

ፖሊስ የመዲናዋንና የኅብረተሰቡን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ እያደረገ ያለውን መልካም ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው የፖሊስ ተቋማትን በብቁ የሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ በማዘመን የሀገርን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራ ስኬታማ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። 

በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በመተባበር አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ መቻላቸውንም ገልጸዋል።   

የሀገር ውስጥና የውጪ ኃይሎች የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ሰላምና ደኅንነት ለማደፍረስ የሚሸርቡትን ሴራ በማክሸፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

አዲስ አበባ ፖሊስ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል እራሱን በማጠናከር ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የመዲናዋን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቁ የሰላም ተምሳሌት ሆናለች ብለዋል።

በዚህም አዲስ አበባ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ስኬታማ በሆነ መንገድ ማከናወን እንድትችል አድርጓታል ነው ያሉት። 


 

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በመዲናዋ በ2016 በጀት ዓመት ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከልና የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ነበሩ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ በቴክኖሎጂና በሰው ሃይል እራሱን በማጠናከር የመዲናዋን ሰላም በአስተማማኝ መልኩ በማስጠበቅ የልማት ስራው እንዲሳለጥ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም የከተማዋን ሰላም በዘላቂነትና በአስተማማኝ መልኩ መጠበቅ መቻሉን ገልጸው፤ የላቀ የስራ አፈፃፀም ያሳዩ የፖሊስ አመራሮችና አባላትን አመስግነዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት ተሸላሚዎች መካከል ኢንስፔክተር ፍቃዱ ነገሰ እና ዋና ሳጅን ተስፋዬ ታረቀኝ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የመዲናዋን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ማስጠበቅ በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። 

የተሰጣቸው እውቅናና ሽልማት በቀጣይ በተቀናጀ መልኩ የመዲናዋን ሰላም ለመጠበቅ መነሳሳት እንደፈጠረላቸውም ነው የተናገሩት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም