በ2017 በሚከናወነው ክልላዊ የመስኖ ልማት ስራ ከ13 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፦ በ2017 በሚከናወነው ክልላዊ የመስኖ ልማት ስራ ከ13 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ የእርሻ መሬት እና የውኃ አቅም እንዳለው ጠቁመው ይህንን ለማልማት ባለፉት ዓመታት የተደረገው ጥረትም አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት ባለፉት ዓመታት ለመስኖ እርሻ ውጤታማነት የሚያግዙ የጄኔሬተር እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱንም አመልክተዋል።


 

በተያዘው የመኸር ወቅት በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎችን በማጠናከር በዘንድሮው የመስኖ እርሻ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በ2017 በሚከናወነው ክልላዊ የመስኖ ልማት ስራ 59 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ13 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ነው አቶ አሻድሊ የጠቆሙት።

በዘንድሮው የመስኖ እርሻ በአቡራሞ ወረዳ መገሌ 39 ቀበሌ 98 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ በመጀመሪያ ዙር እየለማ የሚገኝ የቲማቲም ክላስተር በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።


 

የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በዓመት ሁለት እና ሶስት ጊዜ ማምረትን አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠበቃል ነው ያሉት።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዘንድሮው የመስኖ እርሻ ውጤታማነት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም