የመገጭ ግድብ ግንባታና የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስት ዕድሳት ፕሮጀክቶችን በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ገንብተን እናስረክባለን - ኢዜአ አማርኛ
የመገጭ ግድብ ግንባታና የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስት ዕድሳት ፕሮጀክቶችን በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ገንብተን እናስረክባለን
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፦ የመገጭ መስኖና ንጹህ መጠጥ ውሃ ግድብ ግንባታና የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስት ዕድሳት ፕሮጀክቶችን በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ገንብተው እንደሚያስረክቡ የቤአኤካ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ባለቤት ካሳሁን ምስጋናው ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አመራር ሰጭነት በጎንደር ከተማ ህዝብ ዘንድ የዘመናት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆነው የቆዩት የጎንደር አዘዞ የ12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገድ፣ የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስት ዕድሳትና የመገጭ ግድብ እንዲሁም በመጀመሪያ ዙር የመስቀል አደባባይ - ጃንተከል ዋርካ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች በመፋጠን ላይ ይገኛሉ።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የክልሉ መንግስት የስራ ኃላፊዎች ፕሮጀክቶቹ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት የግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ በመስክ ምልከታቸው አረጋግጠዋል።
የመስክ ምልከታውን ተከትሎም ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።
በዚሁ ጊዜ የቤአኤካ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ባለቤት ካሳሁን ምስጋናው፥ የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስት የዕድሳት ስራን መስራት እንደሚያኮራቸው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በጎርጎራ ልማት ያካበቱት ልምድና ተሞክሮ የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስት የዕድሳት ስራን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ስንቅ እንደሚሆናቸው ነው የተናገሩት።
በዚህም ጎንደር ከተማ ያላትን የቱሪዝም መስህብነትን የሚያሳድግ የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስት የዕድሳት ስራ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ቀን ከሌት እየተሳለጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ ህዝብም ድርጅታቸው እያከናወነ ለሚገኘው የልማት ስራ የሚያደርጉት ያልተቋረጠ ድጋፍ የዕድሳት ስራውን ፈጥኖ ለማጠናቀቅ አቅም እንደፈጠረላቸው አንስተዋል።
በዚህም በጎንደር ከተማ የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስት ዕድሳትና የመገጭ መስኖና ንጹህ መጠጥ ውሃ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ገንብተው እንደሚያስረክቡ ተናግረዋል።
የአፄ ፋሲል አብያተ መንግሥትን የዕድሳት ስራ በጊዜ የለኝም መንፈስ በማጠናቀቅ ለጎንደር ከተማ ውብ ገጽታን በሚያላብስ መልኩ እውን እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።