ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ገቢራዊነት መሰረት የሚጥሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን አድርጋለች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚና የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ ገንቢ ሚና እየተጫወተች መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

15ኛው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የንግድ ሚኒስትሮች ጉባዔ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በዚህ ወቅት፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የጋራ ራዕያችንን የምናሳካበት የበለጸገች አፍሪካን እውን የምናደርግበት ነው ብለዋል።


 

የንግድ ቀጣናው የህጋዊ ንግድ ማሳያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ማቀላጠፍ የሚያስችል ሞተር መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር ቀጣናዊ ትስስር በመፍጠር በአፍሪካ ያለውን ነባራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ በአዲስ መልክ ለማደራጀት መሰረት የሚጥል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ንግድና ኢንቨስትመንትን በማሳደግ አህጉራዊ ትስስርና ትብብር የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።

ነፃ የንግድ ቀጣናውን ገቢራዊ ለማድረግ ውይይት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው፣ በፍጥነት ተግባራዊ በማድረግ ቀጣናዊ ትስስሩን ማቀላጠፍ ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ከንግድ ቀጣናነት ባለፈ የአፍሪካ ዘላቂ እድገት ማረጋገጫ መሆኑን በመግለጽ።

እንደ አህጉር 1 ነጥብ 4 ቢሊየን አፍሪካውያንን የበለጠ በማስተሳሰር ፈጣንና ወደ ብልፅግና የሚያሻግር ኢኮኖሚያዊ እድገት ማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ድህነትን ለመቀነስ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ ፈጥራለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ህጎችና መመሪያዎችን በማሻሻል ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ገቢራዊነት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረች መሆኑንም አንስተዋል።

ይህም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ትግበራ ለማቀላጠፍ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን በመጥቀስ።

አፍሪካ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖዎችን በመቋቋም የኢኮኖሚ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እውን በማድረግ የገበያ ትስስሩን በመጠንና በጥራት ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

የኢኮኖሚ ብዝሀነትና ቅንጅታዊ አሰራርን በማንበር ለቀጣዩ ትውልድ ኢኮኖሚያዊ እድገቷ የተረጋገጠና የበለጸገች አፍሪካን ማስረከብ ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ለዚህ ደግሞ ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ፣ የአህጉሪቱን የኢንዱስትሪ አቅም በቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም