መስማት የተሳናቸው ዜጎች በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
መስማት የተሳናቸው ዜጎች በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፦ መስማት የተሳናቸው ዜጎች በሀገሪቱ በሚከናወኑ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ክንውኖች ዙሪያ ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙ መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ገለጸ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን መስማት የተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መረጃ የማግኘት መብታቸው እንዲረጋገጥ የመገናኛ ብዙሃን ሊኖራቸው ስለሚገባው ሚና ለዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ መስማት የተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ላይ የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶችና ሚዲያዎች ለአካል ጉዳተኞች ያላቸው የመረጃ ተደራሽነት ላይ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዮናስ ፋንታዬ መድረኩ የመገናኛ ብዙሃን በችግሩ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
የመገናኛ ብዙሃን በሚያስተላልፏቸው ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎች እና ፕሮግራሞች መስማት የተሳናቸውን ዜጎችን በምን መልኩ ተደራሽ እያደረጉ መሆኑን መፈተሽ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ውስን የመገናኛ ብዙሃን በሚያቀርቧቸው ፕሮግራሞች መስማት የተሳናቸው ወገኖች መረጃ እንዲያገኙ በሚያስችል መልኩ ቢያቀርቡም በጠቅላላው ሲታይ ብዙ እየተሰራበት አለመሆኑን ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሃን መስማት የተሳናቸው ዜጎች በሀገሪቱ የሚከናወኑ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ክንውኖች ዙሪያ ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙ የማድረግ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃን ልዩ ትኩረት ለሚሹ ወገኖች ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን እንዲሰጡ ለማስቻል ባለስልጣኑ ለዘርፉ ተዋናዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በውይይቱ የተገኙት የህግ ባለሙያው ካልአዩ አያሌው በበኩላቸው በሀገር ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ላይ መስማት ለተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መረጃ የሚሰጡበት ሁኔታ የሚበረታታ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን አንስተዋል።
ይህ ችግር እንዲቀረፍ መገናኛ ብዙሃን ከምንጊዜውም በላይ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መረጃ የሚያገኙበትን አካታች ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።