የአዲስ አበባ ፖሊስ ሕዝብን በማሳተፍ የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት በዘላቂነት የማስጠበቅ ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ፖሊስ ሕዝብን በማሳተፍ የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት በዘላቂነት የማስጠበቅ ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዘመኑ የሚጠይቀውን አሰራር በመከተልና ሕዝብን በማሳተፍ የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት በዘላቂነት የማስጠበቅ ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ በ2016 በጀት ዓመት የላቀ የሥራ አፈፃፀም ላሳዩ የፖሊስ አመራሮች፣ አባላትና ተቋሙ ስኬታማ ተግባር እንዲያከናውን ድጋፍ ላደረጉ አካላት እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል።
በእውቅናና ሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋውና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የመዲናዋና የፌደራል ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፣ በሪፎርሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ በብቁ የሰው ኃይል እንዲደራጅና ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ ተላብሶ እንዲሰራ ተደርጓል።
በዚህም የመዲናዋ ፖሊስ በሥልጠና አቅሙን በማሳደግ ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ተላብሶ እንዲሰራ፣ ተደራሽነቱን እንዲያሰፋ እንዲሁም አሰራሩን እንዲያዘምን ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ የመዲናዋንና የሕዝቡ እንቅስቃሴ ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆን ተልእኮውን በትጋትና በብቃት እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።
ፖሊስ ባለፈው በጀት ዓመት የከተማዋን የሰላምና ደኅንነት ለማወክ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ የልማትና የሰላም ተምሳሌት እንድትሆን ማድረጉን አንስተዋል።
የአዳስ አበባ ፖሊስ ወንጀልን ቀድሞ የመከላከልና የሕግ የበላይነትን የማስከበር አቅሙ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው በቀጣይም ኅብረተሰቡን በማሳተፍና ዘመኑ የሚጠይቀውን አገልግሎት በማሳደግ ሰላምና ደኅንነት የመጠበቅ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ፖሊስ የመዲናዋንና የኅብረተሰቡን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ እያደረገ ያለውን መልካም ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ እንደሚደረግ ከንቲባ አዳነች አረጋግጠዋል።