በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተጠናቀቀ
ቦንጋ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት መጠናቀቁንና የተሰበሰበውን አጀንዳ መረከቡን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር በክልሉ ከጥቅምት 24 ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር መጠናቀቁን አረጋግጠዋል።
እንዲሁም በሀገር አቀፉ ምክክር ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የመምረጥ መድረክ በተሳካ መልኩ መከናወኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ሲካሄድ በቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ላይ ወደ 2 ሺህ 200 የሚጠጉ የማህበረሰብ፣ የተቋማት፣ የማህበራት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች መሳተፋቸውንም ጠቅሰዋል።
ሂደቱ አሳታፊ፣ ፍትሃዊና ሀሳቦች ያለምንም ተፅእኖ የተንሸራሸሩበት መሆኑንም ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ አብራርተዋል።
ይህም ከአጀንዳ ማሰባሰብና ተወካዮችን ከመምረጥ ባለፈ ለአገራዊ ምክክሩ ልምድ የተገኘበትና ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
በተሳታፊዎች የተነሱ አጀንዳዎች ተደራጅተው ለኮሚሽኑ ቀርቦ መረከቡንና ክልሉን በመወከል በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች ምርጫም መካሄዱን አመልክተዋል።
የተወካዮች ምርጫም ግልፅና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ መካሄዱን የጠቀሱት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፣ ለስኬታማነቱ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
በማጠቃለያው ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ሙሉጌታ አጎ እና ዘገዬ አስፋው ተገኝተዋል።