ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን ወደ አክራ በረራ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን ወደ አክራ በረራ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ የመጀመሪያው ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን ወደ ጋና አክራ ከተማ በረራ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰሞኑን በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የA350 -1000 አውሮፕላን ከኤር ባስ ኩባንያ መረከቡ ይታወሳል።
ይህ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራውን ወደ ናይጄሪያዋ ከተማ ሌጎስ ማድረጉ ይታወቃል።
አየር መንገዱ በአፍሪካ የመጀመሪያ በሆነው ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን ወደ ዱባይ ሁለተኛ በረራ ማድረጉም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው መረጃ ሌላኛዋ የምዕራብ አፍሪካ መዳረሻ የሆነችው የጋና ዋና ከተማ አክራ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን በኮቶካ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በድምቀት ተቀብላለች ብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት ባሉት 147 አውሮፕላኖች 140 ዓለም አቀፍና 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.አ.አ በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር ከፍ በማድረግና በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ይገኛል።