ቀጥታ፡

እየተገነባ የሚገኘው የመከላከያ ኃይል ለሀገር ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅሞች መረጋገጥ ዋስትና ነው - አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፦ እየተገነባ የሚገኘው የመከላከያ ኃይል ለሀገር ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅሞች መረጋገጥ ዋስትና ነው ሲሉ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለመከላከያ አዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ ተማሪዎች፣ አመራሮች እና መምህራን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸውም ከሁሉም ሀገራት ጋር ሰላምን እና ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝና ይህንኑ አጠናክሮ በማስቀጠል ኢትዮጵያ በአህጉራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን ተሰሚነት አስጠብቆ ማስኬድ ተችሏል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ማዕከል ያደረጉ የደህንነት እና የዲፕሎማሲ ስራዎች በመሰራታቸው ስኬታማ ውጤት ሊመዘገብ መቻሉንም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ባለው የአፍሪካ ቀንድ እንደመገኘቷ፣ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ብዝኻ ተዋንያን መድረኮች መስራችና ንቁ ተሳታፊነቷ ጎረቤት ሀገራትን በማስቀደም አጋርነትን በማስፋት፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር መስራት የሚያስችል ፖሊሲ ተቀርጾ እየተሰራበት እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የውስጥ ሰላምና አንድነት፣ የሰከነ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር ዋናው የጥንካሬ ምንጭ ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ይህንንም ለማረጋገጥ ብሄራዊ መግባባትን ማጎልበት፣ ድህነትን መቅረፍና አካታችና ፍትሃዊ እድገት ማረጋገጥ፣ እየተለወጠ የመጣውን ዓለማዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ወትሮ ዝግጁነትን እውን ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ይህንኑ ግምት ውስጥ ያስገባ የአስር ዓመት መሪ እቅድ መዘጋጀቱን፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መቀረፁንና ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱን የቻለ የብሄራዊ ደህንነት ፖሊሲ ቀረፃም በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ያለ ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊትና የደህንነት ተቋማት አስተማማኝ ሰላም ማስፈንና ብሄራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ አዳጋች መሆኑን ጠቁመው ኢትየጵያን በሚመጥን ልክ እየተገነባ የሚገኘው የመከላከያ ኃይል ለሀገራችን ሉዓላዊነት እና በሔራዊ ጥቅሞች መረጋገጥ ዋስትና ነው ብለዋል።

አምባሳደር ሬድዋን በገለጻ ማጠቃለያቸው እንደተናገሩት በምግብ ሰብል ራስን ከመቻል ጀምሮ በሁሉም ዘርፍ የህዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ውስጣዊ አንድነትን ለማጠናከር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

የመከላከያ አዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸው በበኩላቸው ኮሌጁ የመከላከያ ሰራዊታችንን ወታደራዊ አመራሮች አቅም ለማሳደግ በአጭር እና በረዥም ኮርስ መርሃ ግብሮች ተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎች እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

በስልጠናዎቹ በመከላከያ ሰራዊት ሁለንተናዊ የማድረግ አቅም ላይ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንም ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸው ተናግረዋል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በኮሌጁ ተገኝተው ለሰጡት ሀገራዊ እና ወቅታዊ ገለጻ በማመስገን የኮሌጁን አርማ በስጦታ ማበርከታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም