የፀጥታ ኃይሉን አቅም በማጎልበትና አሰራሮችን በማዘመን የሀገርን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የፀጥታ ኃይሉን አቅም በማጎልበትና አሰራሮችን በማዘመን የሀገርን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፦ የፀጥታ ኃይሉን አቅም በማጎልበትና አሰራሮችን በማዘመን የሀገርን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ገለጹ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ በ2016 በጀት ዓመት የላቀ የሥራ አፈፃፀም ላሳዩ የፖሊስ አመራሮች፣ አባላትና ተቋሙ ስኬታማ ተግባር እንዲያከናውን ድጋፍ ላደረጉ አካላት እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል።
በመርኃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የፌደራል ፖሊስ ከሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋውና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የፌዴራልና የከተማዋ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት በየደረጃው የሚገኙ የፖሊስ ተቋማትን በብቁ የሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ በማዘመን የሀገርን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራ ስኬታማ ማድረግ ተችሏል።
በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ አካላት በመቀናጀትና በመናበብ እንዲሁም ከህዝቡ ጋር በመተባበር አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ መቻላቸውንም ገልጸዋል።
በዚህም ፖሊስ የሀገር ውስጥና የውጪ ኃይሎች የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ሰላምና ደኅንነት ለማደፍረስ እያደረጉት ያለውን ሴራ በማክሸፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አዲስ አበባ ፖሊስ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል እራሱን በማጠናከር ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በትብብር በመሥራቱ የአዲስ አበባ ከተማን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቅ የሰላም ተምሳሌት እንድትሆን እንዳደረጋት አንስተዋል።
በዚህም አዲስ አበባ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ስኬትማ በሆነ መንገድ ማከናወን እንድትችል ማድረጉን ጠቁመዋል።