ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የህክምና ላቦራቶሪ አገልግሎትን በጥራት ለማዳረስ ትኩረት መደረጉ ተገለጸ

ባህርዳር፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የህክምና ላቦራቶሪ አገልግሎት በጥራት በማዳረስ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመገንባት ትኩረት መደረጉ ተገለጸ።

"ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎት ለማይበገር የጤና ስርዓት" በሚል መሪ ሃሳብ 3ኛው የላቦራቶሪ ፌስቲቫል በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በወቅቱ፤ ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

የጤና ተቋማት ጊዜው የሚጠይቀውን ዘመናዊ የላቦራቶሪ መመርመሪያ መሳሪያዎች እንዲያደራጁ  ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ትክክለኛ የምርመራ ውጤት በአጭር ጊዜ በማውጣት ጥራት ያለው የላቦራቶሪ የምርመራ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስችል አስረድተዋል። 

የፌስቲቫሉ ዓላማም የላቦራቶሪ ጥራትን፣ ተደራሽነትና የህዝብ እርካታን ማረጋገጥ የሚያስችል ንቅናቄ በመፍጠር ሁሉን አቀፍ አቅጣጫዎችን ለማመላከት እንደሆነ አስረድተዋል።

እንዲሁም የላቦራቶሪ ግብዓት አቅራቢዎችና የሚመለከታቸው አካላትን በማገናኘት ለማስተዋወቅ ጭምር መሆኑን አክለዋል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ህክምና ላቦራቶሪ ማህበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አስቴር ፀጋዬ እንዳሉት፤ ላቦራቶሪ የሚከበርና የሚወደድ የሙያ ዘርፍ ነው።

የሀገሪቱን  የጤና ፖሊሲ ለማሳካት ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ የጤናው ዘርፍ አመራር አባላትና ባለሙያዎች ለዘርፉ እድገትና ጥራት መጠበቅ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።


 

የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው፤ የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎት ለህክምናው ዘርፍ የጀርባ አጥንት መሆኑን ገልጸዋል።

የሚሰጡ የላቦራቶሪ አገልግሎቶች ዘመኑን የዋጁና ጥራታቸውን የጠበቁ መሆን እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ለዚህም ብቃት ያላቸው የላቦራቶሪ ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም ጥራትና ብቃት ያላቸውን ላቦራቶሪዎች ማደራጀትና ተደራሽ ማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል።

በፌስቲቫሉ የፌዴራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች፣ ከጤና ተቋማትና ከዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም