ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ገለጹ

ቦንጋ ፤ ጥቅምት 30/2017 (ኢዜአ)፡- ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የአጀንዳ መረጣና የተሳታፊዎች ልየታ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አስተባባሪ አቶ አክሊሉ አለማየሁ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ሀገራዊ ምክክሩ የሚስተዋሉ መሰረታዊ ልዩነቶችን ለመፍታት ዓይነተኛ መሳሪያ ነው።

ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት የውይይት ዕድል እንዳልነበር አስታውሰው፣ ፓርቲያቸው ለምክክሩ ጠቃሚ ነው ብሎ ያመነባቸውን አጀንዳዎች ለይቶ በጋራ መድረኩ ላይ ማቅረቡን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ  ተወካይ ሃምሳ አለቃ ሶሻል አሸናፊ በበኩላቸው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከባለድርሻ አካላት መካከል መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እንደፓርቲ ይጠቅማል ያሏቸውን አጀንዳዎች በነፃነት ማቅረባቸው ሀገራዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል። 

ሁሉም ሀገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩ በሚል እሳቤ ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮችን  በመለየት የመፍትሔው አካል መሆን አለበት ነው ያሉት።

ሀገራዊ ምክክሩ በመንግስትና በሕዝብ መካከል መተማመንን ከማስፈን ባለፈ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በዘላቂነት በመፍታት ሀገራዊ አንድነት ለመፍጠር ወሳኝ በመሆኑ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ፓርቲው ያልተቆጠበ ተሳትፎ ያደርጋል ብለዋል።   


 

የብልጽግና ፓርቲን ወክለው በመድረኩ ላይ የተሳተፉት አቶ መንግስቱ መኩሪያ በበኩላቸው፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባሳተፈ መልኩ የአጀንዳ መረጣና የተሳታፊ ልየታ መደረጉ ሀገራዊ ስብራትን በመጠገን እርስ በርስ መተማመንን ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል ። 

ሁሉም በተሳተፈበት መልኩ አጀንዳ መለየቱ መሰረታዊ የሆኑ አለመግባባቶች ላይ የሚታዩ ችግሮችን በጋራ ተነጋግሮ ለመፍታት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሀገር ከፖለቲካ በላይ መሆኗን ያነሱት አቶ መንግስቱ፣ በመድረኩ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በመከባበርና በመደማመጥ ስሜት ወሳኝ ሀገራዊ አጀንዳዎችን በነፃነት አናሸራሽራለን ብለዋል።

ፓርቲው ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት በትኩረት ከመስራት ባለፈ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማጠናከርና ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ባህል ለማዳበር በቁርጠኝነት ይሰራል ነው ያሉት።


 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ተወካይ አቶ መልካሙ ሸገቶ፣ ሁሉም ተሳታፊዎችና ፓርቲዎች ያለምንም ገደብ ያሏቸውን አጀንዳዎች ማቅረባቸውን  ገልጸዋል።

እንደ ተወካዩ ገለጻ ሀገራዊ ምክክሩ ሠላምን በሚያሰፍኑና የኢትዮጵያን አንድነት በሚያረጋግጡ  ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል። 

ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መምከር  አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ደግሞ፣ የካፋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት ሰብሳቢ አቶ ቦጋለ ኃይሌ ናቸው።

ፓርቲዎችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳዎችን በነጻነት እየሰጡ መሆናቸውን ጠቁመው፣ይህም ችግሮችን ከመለየት ባለፈ የጋራ መፍትሔ ለማበጀት ምቹ መደላድል ይፈጥራል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም