ቀጥታ፡

የኤር ባስ ኩባንያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላል - የኤር ባስ ኩባንያ ዓለም አቀፍ ፕሬዚዳንት 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፦ የኤር ባስ ኩባንያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኩባንያው ዓለም አቀፍ ፕሬዚዳንት ውተር ቫን ዌርስች ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰሞኑን በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የኤ350 - 1000 አውሮፕላን ከኤር ባስ ኩባንያ መረከቡ የሚታወስ ነው።

የኩባንያው ዓለም አቀፍ ፕሬዚዳንት፣ ውተር ቫን ዌርስች ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኤር ባስ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ለረዥም ዓመታት የቆየ ትብብር አለው።  
 

በአፍሪካ ትልቁን የገበያ ድርሻ የሚወስደው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖችን ከኩባንያው በማዘዝም ቀዳሚው አንደሆነ ገለጸዋል።

አየር መንገዱ በየጊዜው አዳዲስ አውሮፕላኖችን እያዘዘ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ ቀደም ሞዴል ኤ350-900 አውሮፕላኖችን መግዛቱን አስታውሰዋል።

አሁን ደግሞ እጅግ ዘመናዊ የሆነውን የኤ350-1000 አውሮፕላን ከኩባንያው መረከቡ በእቅዱ መሰረት እንዲጓዝ የሚያግዘው ይሆናል ብለዋል።

አየር መንገዱ ሰሞኑን ከኤር ባስ ኩባንያ የተረከበው አውሮፕላንም 21ደኛው መሆኑን ገልጸዋል።

የኤር ባስ ኩባንያ በቀጣይም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኤ350-1000 አውሮፕላን በተጨማሪ በትዕዛዝ ላይ ያሉ 11 አውሮፕላኖች መኖራቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ አውሮፕላኖቹን በተያዘለት ጊዜ ለአየር መንገዱ እንደሚያስረክብ ገልጸዋል።

ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አህጉር ያለውን የመሪነት ሚና ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱ እንዲጨምር የሚያደርግ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።

ኤር ባስ ኩባንያ በተያዘው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ብቻ 770 አውሮፕላኖችን ለዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ለማስረከብ እቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ አክለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኤር ባስና ከቦይንግ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች ለመግዛት በትዕዛዝ ላይ ያሉትን 123ቱን በመጪው 6 አመታት ሙሉ ለሙሉ እንደሚረከብ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጸሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ መግለጻቸው ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም