ፋውንዴሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርብቶ አደር አካባቢዎች የግብርና ልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ፋውንዴሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርብቶ አደር አካባቢዎች የግብርና ልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ
ጂንካ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርብቶ አደር አካባቢዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የግብርና ልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤትና የፋውንዴሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ገለጹ።
ፋውንዴሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ወረዳዎች በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የሚተገበር ፕሮጀክት አስተዋውቋል።
"የግብርና ትራንስፎርሜሽን የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትና ፕሮጀክት'' የሚል መጠሪያ ያለው ይኼው ፕሮጀክት በሐመር፣ በና-ፀማይ፣ ዳሰነች እና ኛንጋቶም ወረዳዎች የሚተገበር እንደሆነም ተገልጿል።
በደቡብ ኦሞ ዞን ቱርሚ ከተማ በተካሄደው የፕሮጀክቱ ትግበራ የንቅናቄ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት እና የኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ፤ ፕሮጀክቱ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የግብርና ልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በዋናነት የእንስሳት እና የሰብል ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓቶች እንዲተገበሩ የሚያደርግ ሲሆን፤ የአርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የግብይት ሰንሰለት እንዲኖር እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ወደ ትግበራ ከመግባቱ በፊት በአርብቶ አደሩ አካባቢ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት 79 በመቶ የሚሆኑ አርብቶ አደሮች ስለ ተሻሻለ የእንስሳት ዝርያ በቂ ግንዛቤ እንደሌላቸው የጠቆሙት ወይዘሮ ሮማን፤ በቀጣይ በተሻሻለ የእንስሳት ዝርያዎችና ዘመናዊ የእርባታ ዘዴ ላይ በስፋት የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባር እንደሚከናወን ተናግረዋል።
አካባቢው በተፈጥሮ ሀብትና ፀጋዎች የታደለ ቢሆንም ከዚሁ ሀብት የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አነስተኛ እንደሆነ አንስተዋል።
በዞኑ ካሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አንዱ የኦሞ ወንዝ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በአለም ባንክ ጥናት መሰረት የኦሞ ወንዝ ከ 340 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።
አካባቢው ሰፊ ሊታረስ የሚችል ለም መሬት፣ በቂ የውሃ ሀብትና የሰው ኃይል ያለው በመሆኑ ይህንን አቅም አቀናጅቶ በማልማት የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በቀጣይ የትግበራ ምዕራፉ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በማስተዋወቅና የዘርፉ ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ ከግብርናው ዘርፍ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ምንላርገው አዲሱ በበኩላቸው፤ ፋውንዴሽኑ ያስተዋወቀው ፕሮጀክት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እየተተገበሩ ላሉ የሪፎርም ስራዎች አጋዥ እንደሆነ ገልጸዋል።
የግብርና ትራንስፎርሜሽን የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ወደ ትግበራ ምዕራፍ ከመሸጋገሩ አስቀድሞ በግብርናው ዘርፍ የተሻሻሉ አሰራሮች ላይ ያሉ ችግሮች በጥናት ለይቶ የሚፈታባቸው መንገዶች የማመላከት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
በግብርናው ዘርፍ ከተለዩ ችግሮች በዋናነት የባለሙያዎች አቅም ውስንነት እና በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ስራዎች የግብአት አቅርቦት እጥረት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም እነዚህ ችግሮች ተፈትተው የተሻሻሉ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን ተፈፃሚ ለማድረግ ከፋውንዴሽኑ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።
በተለይ በአካባቢው ያሉ ሀብቶችና ፀጋዎችን በጥናት በመለየት ማልማት የሚያስችል ዕቅድ በመንደፍና በመተግበር የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና ከግብርናው ዘርፍ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ መምሪያው በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ፋውንዴሽኑ የግብርና አሰራርን ለማዘመንና የመረጃ ልውውጥ ተግባርን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ 25 ዘመናዊ ኮምፒውተሮች፣ 25 ዘመናዊ ታብሌቶች እና 25 ፕሪንተሮችን ፕሮጀክቱ ለሚተገበርባቸው ወረዳዎች ድጋፍ ማድረጉ ተመልክቷል።
በየቀበሌው የሚከናወኑ የግብርና ልማት ስራዎችን ለመደገፍ ሞተር ብስክሌቶችንም ፋውንዴሽኑ አበርክቷል።
ከቢል እና ሚሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በደቡብ ኦሞ አራት ወረዳዎች የሚተገበረው ይህው ፕሮጀክት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2024 ተጀምሮ በ2026 እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።