ኢትዮጵያ ባላት የእንስሳት ሃብት ልክ ከወጪ ንግድ ተጠቃሚ እንድትሆን የባለ ድርሻ አካላት ቅንጅት ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ባላት የእንስሳት ሃብት ልክ ከወጪ ንግድ ተጠቃሚ እንድትሆን የባለ ድርሻ አካላት ቅንጅት ሊጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ባላት የእንስሳት ሃብት ልክ ከወጪ ንግድ ተጠቃሚ እንድትሆን የባለ ድርሻ አካላት ቅንጅት ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
የግብርና ሚኒስቴር ከግብርና ባለስልጣን ጋር በመተባበር የስጋ የወጪ ንግድ ላይ በሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የባለድርሻ አካላት ውይይት እያካሄደ ነው።
የግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሃሚድ ጀማል በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ በዓለም ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደብ የእንስሳት ሀብት ቢኖራትም በሚገባት ልክ እየተጠቀመች አይደለም ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 15ሺህ ቶን የእንስሳት ስጋን ወደ ውጭ ለመላክ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተላከው ስጋ ከዕቅዱ አኳያ የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑን ተናግረዋል።
የተሻለ ውጤት ለማምጣት ይበልጥ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ከዶላር አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮች እየተፈቱ መሆኑ ለዘርፉ ትልቅ ተስፋ ይዞ መምጣቱን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ እንስሳት ልማት ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስራት ጤራ በበኩላቸው ከዘርፉ ይበልጥ ለመጠቀም ጥራትን ከማረጋገጥ ባሻገር የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ ቻይና ፍላጎት ማሳየቷን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ እየመጣ ላለው ገበያ የሚመጥን አቅርቦት ለመፍጠር የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።