ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ሕገ- ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር በተከናወነው ስራ አበረታች ውጤት ተገኝቷል - የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ሕገ- ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር በተከናወነው ስራ አበረታች ውጤት መገኘቱን የአዲስ አበባ የሰላምና  ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ እና የኑሮ ውድነትና የዋጋ ማረጋጋት የቁጥጥር ዘርፍ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ  ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ሕገ- ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ ኃይል በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ አመት የዋጋ ንረትን ከመቆጣጠር አኳያ ያከናወናቸው ተግባራትን ገምግሟል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ ሊዲያ ግርማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፤ ያለ ንግድ ፈቃድ መነገድ፣ ንግድ ፈቃድ ያለማደስ፣ ከዘርፍ ውጪ መነገድ፣ ምርት መደበቅ እና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ  በመዲናዋ ተደጋግመው የሚስተዋሉ ሕግ መተላለፎች ናቸው።

ሕገ ወጥ ተግባራቱ ሕብረተሰቡን ከማማረር ባሻገር በሕጋዊ ነጋዴዎች ላይ አላስፈላጊ ጫናዎችን እያሳደሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ግብረ ኃይሉ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት እቅድ በማውጣት ተከታታይ የክትትልና የቁጥጥር ስራዎችን ማከናወኑን አመልክተዋል።

በዚህም ሕገ-ወጦችን ወደ ሕጋዊ መስመር ገብተው የንግድ ስርዓቱን ተከትለው እንዲሰሩ መደረጉን ገልጸው በዚህም በተለይ በሽንኩርት፣ በቲማቲምና በሌሎች ምርቶች ላይ  ትርጉም ያለው ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን ነው የገለጹት።

ማስተካከያ ባልወሰዱ 2 ሺህ 472 በሕገ-ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ የማስጠንቀቂያ እና የማሸግ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አመላክተዋል።

በቀጣይም ግብረ ኃይሉ ቅንጅታዊ ስራውን በማጠናከር ሕገ-ወጦች ላይ ወደ ሕጋዊ መስመር  እንዲገቡ በማድረግ ሕብረተሰቡን ላልተፈለገ ወጪ እንዳይዳረግ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ የንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው ግብረ ኃይሉ በሕገ-ወጥ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ መንገድ እንዲገቡ ከማድረግ አበረታች ውጤት ማስመዘገቡን ገልጸዋል።

በተቋማት መካከል የሚስተዋሉ የቅንጅት ጉድለቶች ሊስተካከሉ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ግብረ ኃይሉ በሩብ አመቱ የዋጋ ንረትን ከመቆጣጠር አኳያ ያከናወናቸው ተግባራትን ገምግሞ 

ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

በአዲስ አበባ ሕገ- ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር በ2015 ዓ.ም ግብረ ኃይል መቋቋሙ ይታወሳል።

ግብረ ኃይሉ በሰላምና ጸጥታ ቢሮ ስር ሆኖ የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮን፣ ፖሊስን፣ ደንብ ማስከበርን፣ ከተማ ግብርናንና ሌሎች ተቋማትን ያቀፈ ነው።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም