ኢትዮጵያ የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥና የሴቶችንና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን አቅም ለማሳደግ እየሰራች ነው - የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥና የሴቶችን፣ የወጣቶችንና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን አቅም ለማሳደግ እየሰራች ነው ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገለጹ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በቺሊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ግላሪያ ዴ ላ ፎንቴ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።


 

ውይይቱ ሁለቱ ሀገራት በሴቶች፣ ወጣቶችና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመደገፍና በማብቃት ረገድ ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።

ሚኒስትሯ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ቺሊ በሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥና የሴቶች፣ የወጣቶችንና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን አቅም ለማሳደግ እየሰራች ነው።

ለዚህም የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በመንደፍ እየተገበረች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከቺሊ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከሯ በዘርፉ በስትራቴጂክ ዕቅዱ የተመላከቱ ተግባራትን በመላ ሀገሪቱ ተደራሽ ለማድረግ ያግዛታል ብለዋል፡፡

በተለይም በገጠር ያሉ ሴቶች በግብርናው መስክ ተሰማርተው ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግና ሰላምን ዘላቂ ከማድረግ አኳያ የሚኖራቸውን ሚና ለማሳደግ ከቺሊ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ገልጸዋል።


 

የቺሊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ግላሪያ ዴ ላ ፎንቴ በበኩላቸው የቺሊ እና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በርካታ ዓመታት ማስቆጠሩን ተናግረዋል።

በመሆኑም ካሁን ቀደም ከነበረው በተሻለ ሁኔታ ግንኙነታቸውን ማጠናከር የሚያስችሉ አዳዲስ ባህሎችና ልምዶችን ማወቅና መማር እንደሚፈልጉም ጠቅሰዋል።

የሴቶችን፣ የወጣቶችንና ሌሎች ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን አቅም ለማጎልበት በሚከናወኑ ተግባራት ላይ በጋራ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም