ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ሥምምነት ማዕቀፍን ለመተግበር የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኗን ተገንዝበናል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና  ስምምነት ማዕቀፍን ለመተግበር የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኗን ተገንዝበናል ሲሉ የ19 ኛው የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስብሰባ ተሳታፊዎች ገለጹ።    

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት አባል አገራት 19ኛው የከፍተኛ የንግድ ኃላፊዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች  በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሚገኘውን የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ማሳያ ኤግዚቢሽን ማዕከል በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል።


 

በማዕከሉ የግብርና ምርቶች፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች ማዕድንን ጨምሮ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ለጎብኚዎቹ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።      

ከጎብኚዎቹ መካከል የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና የቡሩንዲ ተወካይና ዋና ተደራዳሪ ኦኒዚሜ ኒዩኩሪ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በጉብኝቱ የንግድና የአገልግሎት ዘርፉ ለኢትዮጵያ ዕድገት ምን ያህል አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ለመገንዘብ ችያለው ብለዋል።       

ኢትዮጵያ በግብርና፣ በአምራች ዘርፍና በሌሎችም መስኮች የደረሰችበትን ደረጃ ለማወቅ መቻላቸውን ገልጸው፤ እንደዚህ ዓይነት ቋሚ ኤግዚቢሽን የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ ረገድ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።  

በኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን ለመተግበር የሚደረጉ ዝግጅቶችን ተዘዋውሬ ጎብኝቻለሁ ያሉት ዋና ተደራዳሪ ኦኒዚሜ ኒዩኩሪ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ሥምምነትን ለመተግበር የሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኗን ተገንዝቤያለሁ ሲሉ ተናግረዋል።   


 

የላይቤሪያ ንግድ ሚኒስቴር ተወካይ ሪቻርድ ፕራት በበኩላቸው በማዕከሉ የጎበኘናቸው ምርቶች ኢትዮጵያ ሌሎችም የአፍሪካ አገራት ሰፊ የገበያ መዳረሻ መሆን የምትችል አገር መሆኗን የሚያመላክቱ ናቸው።    

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን እውን ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ምሳሌ የሚሆን ሥራ እያከናወነች መሆኑን አይተናል፤ ለሌሎችም አገራት አርአያ የሚሆን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የአፍሪካ አገራት ከሥምምነት ማዕቀፉ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙም የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።  


  

የኬኒያ ተወካይ ፊቢያን ሞታማ በበኩላቸው አብዛኛው የአፍሪካ አገራት ምርቶችን ከውጭ ነው የሚያስገቡት፤ ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት አገራት በራስ አቅም ማምረት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።      

ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ አርአያ የሚሆን ሥራ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ አህጉራዊ አጀንዳ 2063 እውን እንዲሆን ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች መሆኑን መገንዘባቸውንም ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ ያስሚን ወሃብረቢ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ሥምምነት ማዕቀፍ እውን እንዲሆን ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጀምሮ ስትሰራ መቆየቷን  አስታውሰዋል።        

ኢትዮጵያ አሁንም አህጉራዊ ሚናዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።  

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና 15ኛው የንግድ ሚኒስትሮች ስብሰባ የፊታችን ቅዳሜና እና እሁድ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

 

 

      

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም