የዘመነ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት ወደ ሪፎርም ገብተናል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የዘመነ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት ወደ ሪፎርም ገብተናል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2017(ኢዜአ)፦ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የማይፈርስና የዘመነ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት ወደ ሪፎርም መገባቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም አመራር ዐቢይ ኮሚቴ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
የኮሚቴው አባላት በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎችን የጎበኙ ሲሆን በመጀመሪያ ዙር የተካተቱ ስምንት ተቋማት በተገኙበት የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራዎችን ገምግሟል።
ዐቢይ ኮሚቴው ተቋማት ያከናወኗቸውን ተግባራት በዝርዝር በመቃኘት ጥንካሬዎችን፣ ውስንነቶችና በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሥርዓት ከፈጠረች ከ116 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።
ሆኖም በአገልግሎት አሰጣጥ፣በአደረጃጀት፣በአሰራር ሥርዓት፣ በሰው ኃይል ብቃትና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም አሁንም ጥያቄ የሚነሳበት የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር መኖሩን ተናግረዋል።
የመንግሥት ተቋማት አፈጻጸም ደካማ በመሆኑና የአገልግሎትና የአስተዳደር ችግር በመኖሩ ዛሬም ከድህነትና ኋላ ቀርነት አልተላቀቅንም ብለዋል።
የሪፎርሙ መንግሥት የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር እንዲሻሻል፣ ተቋማት የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና እንዲላበሱ ወስኖ ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጸዋል።
በዚህም መንግሥት የአገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ የጸደቀ ሲሆን የማስፈጸሚያ ፍኖተ ካርታም ተዘጋጅቷል ብለዋል።
የአገልግሎትና አስተዳደር አዋጁም በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው አዋጁ ሲጸድቅ ወደ ሪፎርሙ ሙሉ ትግበራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የመንግሥት ተቋማት በሦስት ዙር ተከፍለው ሪፎርሙን እንደሚተገብሩ ገልጸው ሪፎርሙ የዝግጅት፣ የትግበራና የማፅናት ምዕራፍ ዓለው ብለዋል።
መንግሥት ሪፎርሙን ለማድረግ ያስፈለገበት ዋና ዓላማ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሥርዓትን ለማዘመንና በመንግሥታት ለውጥ ፀንቶ የሚቀጥል ሥርዓት ለመገንባት እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በነበሩት መንግሥታት በርካታ ጊዜ ሪፎርሞች ቢሞከሩም በተለያየ ምክንያት አልተሳኩም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጡ መንግሥት ጠንካራ ሥርዓት በመገንባት አሻራውን ለማኖር ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግሥትን አገልግሎት የሚያስፈፅመው የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት መንግሥታትና ፖለቲከኞች በተቀየሩ ቁጥር እየፈረሰ የሚገነባ መሆን የለበትም ነው ያሉት።