የሌማት ትሩፋት ህብረተሰቡ ለዘመናት ሳይጠቀምበት የኖረውን ጸጋ አልምቶ ጥቅም ላይ እንዲያውል አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የሌማት ትሩፋት ህብረተሰቡ ለዘመናት ሳይጠቀምበት የኖረውን ጸጋ አልምቶ ጥቅም ላይ እንዲያውል አስችሏል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2017(ኢዜአ)፦ የሌማት ትሩፋት ህብረተሰቡ ለዘመናት ሳይጠቀምበት የኖረውን ጸጋ በራሱ አልምቶ ጥቅም ላይ እንዲያውል ያስቻለ መርሀ ግብር መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች፣ ሁሉን አብቃይ የአየር ንብረት የታደለች ነገር ግን በሃብቶቿ በአግባቡ ያልተጠቀመች ሀገር ናት፡፡
ይሁን እንጂ በመንግስታት መቀያየር ያላትን እምቅ ሀብት ጥቅም ላይ በማዋል ህዝቦቿን ከጉስቁልና መጠሪያዋን ደግሞ ከድህነት ምሳሌነት የሚፍቅ አሰራር መዘርጋት ሳይቻል ቆይቷል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በድህነት ሲማቅቁ የኖሩት ጸጋቸውን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው እንጂ በማጣት አይደለም፡፡
በኢትዮጵያ ንብ ማነብ፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ማልማት፣ እንስሳትና ዶሮ ማርባት የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ ቢኖርም በቂ የጋራ ግንዛቤ ባለመፈጠሩ ችግሩን መፍታት ሳይቻል ቆይቷል፡፡
የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ሲጀመር ለመልማት ያለውን ጸጋና አስቻይ ሁኔታ እንዲሁም የህብረሰቡን አቀባበል ታሳቢ ያደረገ ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል፡፡
በየዘመኑ የነበሩ መንግስታት ቁርጠኝነትና የህብረተሰቡ ፍላጎት አናሳ መሆን ያለውን የተፈጥሮ ሀብት የማይመጥን ዘገምተኛ ዕድገት እንዲኖር ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡
ለአብነት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት በተጀመረው የእንስሳት ዝርያን የማሻሻል መርሀ ግብር በ70 ዓመት ውስጥ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን እንስሳት መዳቀላቸውን ገልጸዋል፡፡
በአንጻሩ የሌማት ትሩፋት ሲጀመር በዓመት 500 ሺህ የእንስሳት ዝርያ እንደተሻሻለ ገልጸው፤ በ2016 ዓ.ም አሃዙን ወደ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ከፍ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም አንዲት የሀበሻ ላም በቀን የምትሰጠውን በአማካይ ከ 1 ነጥብ 5 ሊትር የማይበልጥ ወተት በተሻሻሉ ዝርያዎች ወደ 15 ሊትር ማሳደግ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ቁርጠኝነት የህብረተሰቡን አመለካከት በመቀየር የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ የተትረፈረፈ ምርት እንዲገኝ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ዜጎች እጃቸው ላይ ያለውን ሀብት አልምተው መጠቀም ባለመቻላቸው ለረሀብ የተጋለጡበትን አሳፋሪ የታሪክ ምዕራፍ መቀየሩን ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለወተት፣ ሥጋ፣ እንቁላል፣ ማር እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ይሰጥ የነበረው ትኩረት አናሳ እንደነበር አስታውሰው፤ በአራት ዓመቱ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የተያዘውን ግብ በሁለት ዓመት ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡
መንግስት በማስተማርና የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት ህብረተሰቡን በማሳተፉ የተጠቃሚዎች ቁጥር እየላቀ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ካላት መልማት የሚችል የተፈጥሮ ሀብት እና ከህብረተሰቡ ፍላጎት አንፃር ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡