ግብርናቸውንም፤ የኑሮ ዘይቤያቸውንም ያዘመኑት ብርቱው አርሶ አደር -ገብሩ ታፈሰ - ኢዜአ አማርኛ
ግብርናቸውንም፤ የኑሮ ዘይቤያቸውንም ያዘመኑት ብርቱው አርሶ አደር -ገብሩ ታፈሰ
አርሶ አደር ገብሩ ታፈሰ በብርቱ አራሽነታቸውና በሞዴል አምራችነታቸው በቀዬው ማህበረሰብ ዘንድ ይታወቃሉ-በተለይ በበቆሎ ምርታቸው።
አቶ ገብሩ በደጃቸው እና እርሻ ማሳቸው ላይ ሁሉን አቀፍ የግብርና ስራዎችን ይከውናሉ።
ነገር ግን የተራቆተ ገላጣማ ማሳቸውን ወደ ፍሬፍሬ ደን ይለውጣሉ ብሎ የጠበቀ የአካባቢው ነዋሪ አልነበረም።
በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ የአብኮ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ገብሩ ታፈሰ ግን በብርቱ ጥረታቸው አደረጉት።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ጀምረው ወንዝ ዳር የሚገኘውን የተራቆተ ማሳ በመንከባከብና ተገቢውን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ በመስራት ቀስ በቀስ ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ማሳ ለወጡት።
ከሶስት ዓመታት በፊት የጀመሩት የፍራፍሬ ልማት ዛሬ ከራሳቸው ፍጆታ አልፎ ምርታቸውን ለገበያ እያቀረቡ ነው።
በመኸር ሰብል ብቻ ላተኮረው የአካባቢው ማህበረሰብም የተሞክሮ ማዕከል በመሆን ሙዝን ጨምሮ በስፍራው ያልተለመዱ አትክልቶችና ፍራፍሬ አይነቶች እንዲስፋፉ በማድረግ ዐይን ገላጭ ሆነዋል።
"ከሁለት ዓመታት ወዲህ ባየሁት የተትረፈረፈ ምርት እስከዛሬ ማሳዬን አልምቼ ባለመጠቀሜ በጣም ይቆጠኛል" ይላሉ።
አቶ ገብሩ ማሳቸው ብቻ ሳይሆን ደጃቸው የብርቱ ገበሬ አሻራ ይነበብበታል።
በመኸር በጋ መስኖም ሰብሎችን በስፋት ከማምረት ባለፈ የሰንጋ በሬ ያደልባሉ፤ የሌማት ቱርፋት ግብዓት የሆኑ ከዶሮ እስከ ወተት ላም ያረባሉ፣ የራሳቸው ወፍጮ ቤት አቋቁመው ይሰራሉ።
በበሬ ብቻ ሳይሆን በትራክተር በመታገዝ ሰፋፊ እርሻ የሚያለሙ አርአያ ሰብ ናቸው።
አርሶ አደር ገብሩ ከራሳቸው አልፈው ሌሎች የቀያቸው ነዋሪዎች በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሰማሩ ተሞክሯቸውን ያጋራሉ።
አቅማቸው በፈቀደው ልክም የግብርና ግብዓት እገዛ ያደርጋሉ።
በመንግሰት በተሰጠው ትኩረት በመመራት እና የእርሳቸውን ፈለግ ተከትለው በፍራፍሬና ሌሎች ልማቶች የተሰማሩ አርሶ አደሮች ውጤታማ መሆናቸውን ያነሳሉ።
ብርቱው አርሶ አደር ገብሩ ታፈሰ ዕውን ያደረጉት ታዲያ የተቀናጀና የዘመነ ግብርና ስራን ብቻ አይደለም።
ይልቁኑም ባዘመኑት ግብርና በመመራት የገጠር የኑሮ ዘይቤያቸውንም አዘምነዋል። የሰውና እንስሳት የመኖሪያ ቤት በመለየት፣ መጸዳጃ ቤት በመገንባትና የቤት አያያዝን በማሻሻል በምሳሌነት ይጠቀሳሉ።
"ምንም የአርሶ አደር ቤት ቢሆን የተሻለና ፅዱ አኗኗር እንከተላለን" ሲሉ የገጠር ኮሪደር ዓላማ ጋር የሚጣጣም ስራቸውን ይገልጻሉ።
"ከጨውና ዘይት በስተቀር የምንገዛው የለም" ከምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ባሻገር ከገጠር እስከ ከተማ የተሻለ ሀብት የማፍራት፣ ልጆችን የማስተማርና ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት የመምራት ህልም እንዳሳኩ ይገልፃሉ።
የአበሽጌ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አብዱልከሪም ናስር እንደሚሉት አርሶ አደር ገብሩ የተራቆተ መሬትን እንዲያገግም በማድረግና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ያመጡት ለውጥ ለሌሎች አርዐያ የሚሆን ነው።
የነ አቶ ገብሩ አካባቢ በቦቆሎ እንጂ በሙዝ ፍራፍሬ ልማት እምብዛም እንደማይታወቅ አስታውሰው፤ በከልሉ በመጀመሪያ ዓመት 30፣ በሁለተኛው ዓመት 40 እና በሶስተኛው ዓመት 30 የፍራፍሬ ችግኞችን የመትከል ኢኒሼቲቭ ግን አርሶ አደሮችን ወደ ፍራፍሬ ልማት በማስገባት የነበረውን አስተሳሰብ መለወጥ እንደተቻለ ጠቁመዋል።
አቶ ገብሩን ጨምሮ በወረዳቸው ለገጠር ኮሪደር ልማት ምሳሌ የሚሆኑ አርሶአደሮች እንዳሉ በማውሳት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማትን በሁሉም ዘንድ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ቱርፋት፣ ውብና ፅዱ አካባቢን በመፍጠር እንዲሁም ዘመናዊ የኑሮ ዘይቤን በማስፋት የገጠር ኮሪደር ልማትን ዕውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።