በተያዘው በጀት ዓመት ለውጭ ከሚቀርብ የቡና ምርት 2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በተያዘው በጀት ዓመት ለውጭ ከሚቀርብ የቡና ምርት 2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2017(ኢዜአ)፦ ጥራት ያለው የቡና ምርትን በማሳደግ፣ እሴት በመጨመር እንዲሁም የገበያ አማራጮችን በማስፋት በበጀት ዓመቱ ከቡና ወጪ ንግድ 2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለፀ።
ባለፉት ስድስት ዓመታት ቡና ከአረንጓዴ አሻራ ጋር ተሳስሮ በመተከሉ ምርቱ በየዓመቱ በአማካይ በ100 ሺህ ቶን እየጨመረ መምጣቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያሳያል።
በዚህም ባለፈው በጀት ዓመት ከቡና የወጪ ንግድ 1 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን በመጠቆም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ የቡና ምርትን በብዛትና በጥራት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ያላትን ደረጃ ከፍ እንደምታደርግ በቅርቡ መናገራችው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ባለሥልጣኑ በ2017 በጀት ዓመት ብዛትና ጥራት ያለው ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ከፍ ለማድረግ አቅዶ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።
በተያዘው በጀት ዓመት ከ400 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት መታቀዱን ጠቅሰው ባለፉት ሦስት ወራት 115 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ 520 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ተናግረዋል።
በሦስት ወራት የተገኘው የውጭ ምንዛሬ በበጀት ዓመቱ ለማግኘት የታቀደውን የሁለት ቢሊየን ዶላር ገቢ ዕቅድ ማሳካት እንደሚቻል አመላካች ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የቡና ምርትና ምርታማነትን መጨመር እንዲሁም ጥራት ያለው ቡና ወደ ገበያ ለማቅረብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በእዚህም የአረጁ የቡና ተክሎችን በማንሳት በአዲስ የመተካት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
ጎን ለጎንም የቡና ግብይቱን የሚያሳልጡ አሰራሮችን የመዘርጋትና የገበያ አማራጮችን የማስፋት ሥራዎች በሥፋት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በቡና ምርት እሴት የመጨመርና የግብይት ሰንሰለቱን የማሳጠር ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
አርሶ አደሮችና ላኪዎች በማኅበር ተደራጅተው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ የሚያስችል የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም የቡና አምራቾች ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን የሚቆጥብ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እንዲከተሉ የገንዘብና የሙያ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።
በቡናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት አምራቾችና ላኪዎችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር ማድረጉን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን ተፈላጊነት ማሳደግ የሚያስችል ብራንድ የማስተዋወቅ ሥራ በሰፊው መሠራቱን ጠቅሰው ይህም የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆን ማስቻሉን ተናግረዋል።
ጀርመን፣ ጃፓን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ቤልጂየምና አሜሪካ የኢትዮጵያ የውጭ የቡና ገበያ መዳረሻ ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያና ጆርዳን የኢትዮጵያን ቡና በስፋት የሚገዙ ሀገራት እየሆኑ መምጣታቸውን ገልፀዋል።