ቺሊ በአፍሪካ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ቁልፍ አጋር ማድረግ እንደምትፈልግ ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ቺሊ በአፍሪካ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ቁልፍ አጋር ማድረግ እንደምትፈልግ ገለጸች
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 29/2017(ኢዜአ)፦ቺሊ ኢትዮጵያን ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በአፍሪካ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ቁልፍ አጋር ማድረግ እንደምትፈልግ የቺሊ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግሎሪያ ዴ ለ ፎንቴ ጎንዛሌዝ ተናገሩ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፥ በኢትዮጵያ ጉብኝት ካደረጉት የቺሊ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግሎሪያ ዴ ለ ፎንቴ ጎንዛሌዝ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ አምባሳዳር ምስጋኑ፥ በኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዘርፍ እየተመዘገበ ባለው ፈጣን ዕድገት እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፤ በቀጣናዊ እና አካባቢው ባለው የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትኩረት ከሰጣቸው መካከል የግብርና እና የማዕድን ዘርፎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ አክለውም፥ ቺሊ በግብርናእና ማዕድን ዘርፎች ታዋቂ በመሆኗ ኢትዮጵያ ተሞክሮ መቅሰም አንደምትፈልግ ገልጸው፤ የቺሊ ባለሀብቶችምበ በእነዚህ መስኮች እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ የቺሊ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የቺሊ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነ ግሎሪያ ዴ ለ ፎንቴ ጎንዛሌዝ በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግ አረጋግጠዋል።
ቺሊ ኢትዮጵያን ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በአፍሪካ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ቁልፍ አጋር ማድረግ ትሻለች ነው ያሉት።
ባለፈው ዓመት የተካሄደው የሁለትዮሽ የፖለቲካ ምክክር ግንኙነቱ በብዙ ዘርፎች ላይ እንዲያተኩር ቁልፍ ሚና መጫወቱን በማስታወስ።
ሁለቱ ወገኖች ኢትዮጵያ እና ቺሊ በደቡብ ደቡብ ትብብር የበለጠ በጋራ ተቀራርበው በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያም መክረዋል።
ኢትዮጵያ እና ቺሊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 80ኛ ዓመት በቀጣይ ዓመት በጋራ ለማክበር ዝግጅት ለማድረግ መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።