የሲሚንቶ አምራቾች 20 ሚሊዮን ቶን ዓመታዊ ፍላጎትን ለማሟላት በትኩረት መሥራት አለባቸው - ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሲሚንቶ አምራቾች 20 ሚሊዮን ቶን ዓመታዊ ፍላጎትን ለማሟላት በትኩረት መሥራት አለባቸው - ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ አምራቾች 20 ሚሊዮን ቶን ዓመታዊ ሀገራዊ ፍላጎትን ለማሟላት በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከሲሚንቶ አምራቾች ጋር
የሲሚንቶ ምርት አቅርቦት እና ፍላጎት ማጣጣም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል።
ሚኒስትሩ በፍጥነት እያደገ ባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፉ ድርሻ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ይሁንና ለዘርፉ ስራ ቁልፍ የሆነው የሲሚንቶ ዓመታዊ አቅርቦቱ ከ7 ሚሊዮን ቶን አለመዝለሉን አመልክተዋል።
አምራቾች በአቅርቦት በኩል ያለዉን ማነቆ ለመፍታት የማምረት አቅማቸውን ወደ 80 በመቶ በማድረስ 20 ሚሊዮን ቶን ሀገራዊ የሲሚንቶ ምርት ዓመታዊ ፍላጎትን ለማሟላት በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ከዚህ ቀደም በሚኒስቴሩ በኩል ይደረግ የነበረው የሲሚንቶ ግብይት ትስስር ሥራ ከዛሬ ጀምሮ መቅረቱን ጠቁመዋል።
አምራቾች በራሳቸው ኃላፊነት በሚመርጧቸዉ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች በኩል ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።
መንግስት የሲሚንቶ ገበያውን ለማረጋጋት ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የአፈጻጸም ሪፖርት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በማያቀርቡ በማናቸውም የሲሚንቶ አምራች ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
አዲሱን የመንግስት ውሳኔና አቅጣጫ ተከትሎ በግብይት ሰንሰለቱ የደላላ ጣልቃ ገብነት የከሰመ ፣ ለመንግስት ፕሮጀክቶችና ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ አስተማማኝ የሲሚንቶ አቅርቦት የተረጋገጠ እንዲሆን እና አምራቾችም ተገቢውን ትርፍ እያገኙ የፋብሪካዎቻቸውን ዘላቂ ዕድገት እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል።
የግብይት ስርዓቱም ሙሉ በሙሉ ከጥሬ ገንዘብ ክፍያ ነጻ ሆኖ በዲጂታል ክፍያ ሥርዓት እንዲፈጸም አቅጣጫ ተቀምጧል።
የንግድ ሥርዓትና ላይሰንሲንግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ(ዶ/ር) በበኩላቸው የተረጋጋ የሲሚንቶ ምርት ግብይት ሥርዓት ለማስፈን የተደረገው ማሻሻያ የአምራቹንም ሆነ የሸማቹን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ በትኩረት ተግባራዊ መደረግ አለበት ብለዋል።
አምራቾቹ በሙሉ አቅም አምርተዉ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች አቅርቦቱን ተደራሽ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት ሲሚንቶ አምራቾች በአግባቡ እንደሚተገብሩ ገልጸዋል።
አምራቾቹ የማምረቻ ግብዓት፣ የኃይል አቅርቦትና ተያያዥ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።