የኢትዮጵያ አየር ኃይል የበረራ፣ የሥልጠናና የጥገና አቅም ልምድ የሚወሰድበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የበረራ፣ የሥልጠናና የጥገና አቅም ልምድ የሚወሰድበት ነው
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 29/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር ኃይል የበረራ፣ የሥልጠናና የጥገና አቅም ልምድ የሚወሰድበት እንዲሁም ለአፍሪካ የዘርፉ ባለሙያዎች የሙያ ድጋፍ የሚገኝበት ተቋም መሆኑን የሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮ ተናገሩ።
የሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮና የጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪ ባህ በትላንትናው ዕለት የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ጎብኝተዋል።
ለሁለቱ አገራት መሪዎች የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በጉብኝቱ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)ና የአየር ኃይሉ አመራሮች ተገኝተዋል።
መሪዎቹ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሰው ኃይል፣ በትጥቅና ምቹ የሥራ ከባቢን ለመፍጠር ያደረጋቸውን ሪፎርሞች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮ ጉብኝቱን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ እየሰራች ያለው ሥራ ልምድ የሚቀሰምበት መሆኑን አንስተዋል።
በጉብኝታቸው የአየር ኃይሉን የማብረር አቅም ብቻ ሳይሆን በሥልጠናና በጥገና ሥራዎችም ከፍተኛ አቅም እንዳላት መገንዘብ መቻላቸውን አስረድተዋል።
አየር ኃይሉ ያካበተው ልምድና አሁን የደረሰበት የእድገት ደረጃ ለአፍሪካ አገራት የዘርፉ ባለሙያዎች ሥልጠና የሚያገኙበት እድል የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው፤ መሪዎቹ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ሁለቱን ተቋማት እንዲጎበኙ መደረጉን ጠቁመዋል።
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግሥት ለፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ሪፎርም በሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያን ከፍታ የሚመጥንና ትውልድ የሚያኮራ አየር ኃይል መገንባቱ ለመሪዎቹ ተገልጾላቸዋል ብለዋል።
የመሪዎቹ ጉብኝት ኢትዮጵያ ለወዳጅ አገራት ያላትን ልምድ ለማካፈል ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው ይህም በጋራ የመበልጸግ ፍለጎቷ ማሳያ መሆኑን ነው ያነሱት።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው፤ ባለፉት ስድስት አመታት በአየር ኃይል ውስጥ በርካታ ተቋማዊ ሪፎርሞች ሲደረጉ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በተለይም በሰው ኃይል ግንባታ፣ በውጊያ መሰረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂና አጠቃላይ ኢትዮጵያን የሚመጥን አይር ኃይል በመገንባት ረገድ አበረታች ሥራዎች መከናወኑን አስረድተዋል።
ይህም አጠቃላይ የአገሪቱን የዝግጅት አቅም ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።