መንግስት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ጅምር ስራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ጅምር ስራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 29/2017 (ኢዜአ)፦መንግስት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ጅምር ስራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፤ ስራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና በዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (ILO) የጋራ ትብብር ውጤታማ የሥራ ላይ ልምምድ እና ትግበራን አስምልክቶ የተዘጋጀ ውይይት ተካሄዷል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ፣ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ሚኒስቴሩ ሥራ ፈላጊዎች በኢንዱስትሪው ውስጥ ተግባራዊ ክህሎት እንዲያገኙ የሚያግዝ የአሰራር ሥርዓትን ለመዘርጋት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ሚኒስቴሩ የሥራ ላይ ልምምድ መመሪያ ማፅደቁን ማፅደቁንና የሕግ ማዕቀፉ በዓለም የሥራ ድርጅት የሥራ ላይ ልምምድ ጥራትን አስመልክቶ ካስቀመጠው ምክረ ሃሳብ ጋር የሚናበብ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
ተናባቢነቱ የሥራ ልምምዱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ለተለማማጅ ሰልጣኞች እሴት ተጨማሪ የሆነ ልምድ እንዲያገኙ ዕድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የሥራ ገበያው በሚፈልገው ደረጃ ሰልጣኞችን ለማብቃት የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን መደገፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።
መንግስት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ጅምር ስራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑንም አመልክተዋል።
በውይይቱ ላይ የዓለም የሥራ ድርጅት ከአሰሪዎች ፌዴሬሽንና ከመንግስት ጋር በመተባበር እየተገበራቸው ያሉ ፕሮጀክቶች በውይይቱ ላይ ቀርበዋል።
የመጀመሪያው ፕሮጀክት “ፕሮ አግሮ” የሚል ስያሜ ያለው ነው። በዶሮ እርባታ ዘርፍ 200 የሚሆኑ ወጣቶች የስራ ልምምድ እያደረጉበት ይገኛል።
“ፕሮስፔክት” የተሰኘው ፕሮጀክት በብየዳ እና በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዘርፍ 300 የሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ በማድረግ ላይ ናቸው።
በመድረኩ ላይ የዓለም የሥራ ድርጅት፣የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የአይ ሲ ቲ ፓርክ፣ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽንን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ እና አጋር አካላት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።