ቀጥታ፡

ቅርሶች በታሪካዊ ምስክርነታቸውና በሀገር ሃብትነታቸው ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2017(ኢዜአ)፦ ቅርሶች በታሪካዊ ምስክርነታቸውና በሀገር ሃብትነታቸው ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተጠብቀው እንዲተላለፉ እየተሰራ ነው፡፡ 

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፤ ክልሉ የበርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ መስህቦች መገኛ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡ 

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ( ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸው ዓለም አቀፍ ቅርሶች መካከል የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና የፄ ፋሲል ግንብ የሚገኙት በክልሉ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በክልሉ ለቱሪዝም መዳረሻነት የሚያገለግሉ በርካታ ገዳማት፣ ፓርኮችና ሀይቆች እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡ 

እነዚህ ቅርሶች ይዘታቸውን ሳይለቁ ተጠብቀው እንዲቆዩና ለቱሪዝም አገልግሎት እንዲውሉ የሚያደርጉ የመጠበቅ፣ የመንከባከብና የማልማት ስራን በትኩረት እየሰሩ መሆኑን አስታውቋል ፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ በከተማዋ የሚገኙ ጥንታዊ የለገ ኦዳ እና የቦርክቢክ ዋሻ ፣ የግድግዳ ላይ ስዕሎች እና ቤተ እምነቶች ኪነ ህንጻ በብሄራዊ ደረጃ በቅርስነት መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ለድሬዳዋ ከተማ መመስረትና መስፋፋት የድሬዳዋ ምድር ባቡር ትልቅ አስተዋጾኦ ማድረጉ የማይዘነጋ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የምድር ባቡርን ተርሚናል በቅርስነት ለማቆየት የሚያስችል ጥገና  እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡  

ቅርስ የአንድ ማህበረሰብ መገለጫ ከመሆኑም ባለፈ አንድን ማህበረሰብ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር በማገናኘት ያላቸውን ልምድ፣ ባህልና እውቀት እንዲለዋወጡ የሚያደርግ ነው ፡፡ 

ቅርስ ካለው አገራዊ ፋይዳ ባሻገር ዜጎች በዘርፉ ተሰማርተው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ላቅ ያለ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ማህበረሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው ፤ ቅርሶች በታሪካዊ ምስክርነታቸውና በሀገር ሃብትነታቸው ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተጠብቀው እንዲተላለፉ እየሰራን ነው ብለዋል ፡፡ 


 

በሀገሪቱ ከሚገኙ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በመሆን ቅርስን በሳይንሳዊ መንገድ የመመዝገብ፣ የመከታተል፣ የመንከባከብና የማልማት ስራ በቅንጅት እያከናወኑ መሆኑን አመላክተዋል ፡፡

ኢትዮጵያ 12 የሚዳሰሱና 5 የማይዳሰሱ በአጠቃላይ 17 ቅርሶችን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም(ዩኔስኮ) በማስመዘገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት ፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም