ኢትዮጵያ በባህልና ስፖርት ዘርፍ ያላትን እምቅ ሀብት ለዓለም በመሸጥ ወደ ውጤት መቀየር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በባህልና ስፖርት ዘርፍ ያላትን እምቅ ሀብት ለዓለም በመሸጥ ወደ ውጤት መቀየር ይገባል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 29/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በባህልና ስፖርት ዘርፍ ያላትን እምቅ ሀብት ለዓለም በመሸጥ ከውጤቱ ተጠቃሚ ለመሆን በትጋት መስራት ይገባል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሸንካ ገለጹ።
ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከክልልና ከተማ አስተዳደር አመራሮች ጋር በፖሊሲና ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እያደረገ ነው።
በምክክር መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሸንካ፥ኢትዮጵያ በባህልና ስፖርት ዘርፍ ያላትን እምቅ ሀብት ለዓለም በመሸጥ ከውጤቱ ተጠቃሚ ለመሆን በትጋት መስራት ይገባል ብለዋል።
ግጭትን ለመፍታትና ሰላምን ለማስፈን የጥበብ ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ኪነ ጥበብን፣ ስነ ጥበብን እና ባህላዊ እሴቶችን ለሀገር ገፅታና ለትውልድ ግንባታ እንደ ትልቅ መሳሪያ መጠቀምን አዳብረን እንቀጥላለን ብለዋል።
መድረኩ በሃገር አቀፍ ስፖርት ልማት አንፃር የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በተከለሰ የስፖርት ፖሊሲና ረቂቅ የስፖርት አዋጅ፣ በ2017 አንደኛ ሩብ ዓመት አፈፃፃም እና በሌሎች ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክር ተገልጿል።
ባህል፣ ኪነ ጥበብና ስነ ጥበብን ለህዝቦች አብሮነትና ገፅታ ግንባታ ለመጠቀም ያለመ የ3 ወር ንቅናቄ ማስጀመርም ሌላው የመድረኩ ዓላማ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።