ቀጥታ፡

የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የግብርና ወጪ ንግድ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2017 (ኢዜአ)፦ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የግብርና ወጪ ንግድ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ጥሪ አቀረቡ።

ኢትዮጵያ በቻይና ዓለም አቀፍ የገቢ ንግድ ኤክስፖ ጎን ለጎን በተካሄደው የቻይና የገቢ ምግብ ግብአቶች ጉባኤ ላይ ተሳትፎ አድርጋለች።

ኤክስፖ እና ጉባኤው የተዘጋጀው በቻይና የንግድ ምክር ቤት ነው።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ ወደ ቻይና እየላከቻቸው ያሉ የወጪ ምርቶች በየጊዜው እየጨመሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

የቻይና ባለሀብቶች የኢትዮጵያን ምርቶች የመግዛት ፍላጎት ማደጉንም አመልክተዋል።

ቤጂንግ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የግብርና ወጭ ምርቶችን የማስተዋወቅና ከገዢዎች ጋር ለማገናኘት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለመስራት ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶች ጥሪ ያቀረቡት አምባሳደሩ፥ የተለያዩ ማበረታቻዎች እንደተዘጋጁ መግለጻቸውን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም