ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ  የኮንጎ  አየር መንገድን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት አጠናቋል -አቶ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 29/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ  የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ  ሪፓፕሊክ አየር መንገድ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንደሚያስገባው  የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፣አየር መንገዱ በራዕዩ መሰረት ሊደርስበት ያቀደው ደረጃ ላይ ለመድረስ በሁሉም አቅጣጫ በፈጣን የእድገት መንገድ ላይ ይገኛል።

በተለይ የአፍሪካ አየር መንገዶችን በማቋቋም ረገድ አየር መንገዱ ሰፊ ተሞክሮ እንዳለውና በቅርቡም በኮንጎ ኪንሻሳ አዲስ አየር መንገድ ለማቋቋም ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ እንዲሁም የኮንጎ መንግስት 51 በመቶ ድርሻ በመያዝ በመጨው ህዳር ወር መቀመጫውን ኪንሻሳ ላይ ያደረገ አዲስ አየር መንገድ ወደ ስራ እንደሚገባ ነው ያስታወቁት።

የኤር ኮንጎን አየር መንገድ የማስተዳደር ሃላፊነትም ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

አየር መንገዱ የመጀመሪያ አገልግሎቱን በሁለት አውሮፕላኖች በሀገር ውስጥ በረራ እንደሚጀምርና ከስድስት ወር በኋላ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር በመጨመር ወደ ጎረቤት ሀገራት በረራ ይጀምራል ብለዋል።

የኮንጎ ህዝብ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ በአገሪቱ ያለው የአየር ትራንስፖርት ፍላጎት የላቀ መሆኑን ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ገበያ ትርፋማነት ወሳኝ ስራ እንደሚሆን አክለዋል።

በመሆኑም አየር መንገዱን በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች አየር መንገዶቻቸውን እንድናቋቁምላቸው ጥያቄ እያቀረቡ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ከሃገራቱ ጋር ለመስራት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ እንደሆነም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀደም ብሎ ፣ በቶጎ አየር መንገድ አስካይ ኤር ዌይስ፣ በማላዊ ማላዊ ኤርዌይስ፤ በዛምቢያ ዛምቢያ ኤር ዌይስን በማቋቋም ድርሻ ይዞ እየሰራ መሆኑንም አክለዋል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት ባሉት 147 አውሮፕላኖች 140 ዓለም አቀፍና 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.አ.አ በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር ከፍ በማድረግና በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም